የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባሕልና ቋንቋ ምርምር ተቋም ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት፣ ከቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም ከባህልና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው 9ኛው ዓለም አቀፍ የሀገር በቀል ዕውቀት ሲምፖዚየም መጋቢት 19/2018 ዓ/ም ተካሂዷል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ ዓለማችን በአሁኑ ወቅት ታሪካዊና ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ገልጸው፣ የሚታዩትን የአካባቢ ተግዳሮቶች፣ የእርስ በእርስ ግጭቶች እና ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት ሀገር በቀል ዕውቀቶች ዘላቂ መፍትሔ በመስጠት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ አስገንዝበዋል። እነዚህን ዕውቀቶች በሳይንሳዊ መንገድ በአግባቡ መሰነድ የሀገርን ባህልና ቅርሶች ከጥፋት ከመጠበቅ ባለፈ ለትውልድ ለማሻገር የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም፣ ይህ ሲምፖዚየም የጋሞ "ዱቡሻ ዎጋ" በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) በማይዳሰሱ ቅርሶች እንዲመዘገብ የስነዳ ሥራው ተጠናቆ የቫሊደሽን ወርክሾፕ በሚዘጋጅበት ዋዜማ ላይ መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል። ዩኒቨርሲቲው እነዚህን ዕውቀቶች በምርምርና ጥናት ላይ ተመስርቶ በመሰነድና በማልማት ረገድ በትጋት እየሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታሪኩ ኦይቻ ባደረጉት ንግግር፤ የጋሞ "ዱባሸ ዎጋ" ሥርዓት በዩኔስኮ (UNESCO) የዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ እንዲመዘገብ እየተደረገ ለሚገኘው ጥረት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ላበረከተው ከፍተኛ የጥናትና የስነዳ ድርሻ ምስጋና አቅርበዋል። አቶ ታሪኩ አክለውም፣ ትናንትና ዛሬ ያሉ የሀገር በቀል ዕውቀቶች በምርምርና በጥናት ታግዘው ለተተኪው ትውልድ እንዲሸጋገሩ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል። በክልሉ የሚገኙ ልዩ ልዩ ባህላዊ እሴቶችና ዕውቀቶች በዘላቂነት ተሰንደው እንዲቀመጡ ምርምር ከሚያደርጉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ መሥራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ የሀገር በቀል ዕውቀቶች የአብሮነት፣ የአንድነትና የሰላም እሴቶችን በመገንባት ረገድ ያላቸውን ሚና ወደፊትም አጠናክሮ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የዕለቱ ቁልፍ መልእክት አቅራቢ ተመራማሪና ደራሲ አቶ አብዱልፈታህ አብደላህ በበኩላቸው፤ ያደጉት ሀገራት ዛሬ ለደረሱበት ልማትና ብልፅግና መሠረቱ የገዛ ሀገር በቀል ዕውቀታቸውን በአግባቡ መጠቀማቸው መሆኑን ጠቁመዋል። እንደ ሀገር የምንመኘውን ብልፅግና ለማምጣት እነዚህን ዕውቀቶች መተው ሳይሆን ማልማት ይገባል ብለዋል። አሁንም ድረስ የሀገሪቱ ሥርዓተ ማኅበር በአብዛኛው በሀገር በቀል ዕውቀት የሚመራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አብዱልፈታህ፤ ዕውቀቱን ማጥናት ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ለቱሪዝም ልማት፣ ለብሔራዊ መግባባት፣ ለፍትህ መስፈን፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለግብርና ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል። "የምትሄድበት እንዳይጠፋህ የመጣህበትን አትርሳ" በማለትም የቀደሙ ዕውቀቶችን ጠብቆ ማቆየት ለነገው ጉዞ መሠረት መሆኑን ተናግረዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር አቶ ተፈሰ ዋልኤ በበኩላቸው፤ ተቋሙ በአካባቢው የሚገኙ ቋንቋዎችንና ሀገር በቀል ዕውቀቶችን የማልማትና የመሰነድ ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም፣ በአካባቢው የሚገኙ ዕውቀቶችንና ቅርሶችን ለትውልድ ለማስተላለፍ ቤተ-መዘክር (Museum) ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑንና እየጠፉ የሚገኙ ቋንቋዎችን ከጥፋት ለመታደግ የተጀመረው የመሰነድ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። በሲምፖዚየሙ ላይም ስምንት (8) የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት የተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይም ለሲምፖዚየሙ ስኬታማነት ጥናታዊ ጽሁፎችን ያቀረቡ ተመራማሪዎችና ተባባሪ አካላት የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የጥበብ ምንጭ /Spring of Wisdom
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት





