አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት የእግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ከጋሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር ከደቡብ ክልል ለተወጣጡ በሥራ ላይ ያሉ አሠልጣኞች ከኅዳር 20 - 29/2015 ዓ.ም ሲሰጥ የነበረው የ‹‹CAF D License›› የእግር ኳስ አሠልጣኝነት ሥልጠና ተጠናቋል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የCAF ከፍተኛ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ሥልጠናው እግር ኳስ ሳይንሳዊ መሠረት የያዘ፣ ተከታታይነት ያለው፣ በዕውቀት ላይ የተመረኮዘ እና በእቅድ የሚመራ እንዲሆን የሚያስችል ነው ብለዋል። በታዳጊ ሕፃናት ላይ መሥራት ለስፖርት እድገት ያለው ፋይዳ ጉልህ በመሆኑ ሠልጣኞች ወደ መጡበት ሲመለሱ በንድፈ ሃሳብ እና በተግባር የወሰዱትን ሥልጠና በሥራ ላይ እንዲያውሉ ኢንስትራክተሩ አሳስበዋል፡፡

የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ደመላሽ ይትባረክ ሥልጠናው በታዳጊ ልጆች ላይ የሚሠሩ አሠልጣኞችን ክሂሎት እንደሚያሳድግ ተናግረው በቀጣይ በሌሎች የክልሉ ዞኖች እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

የጋሞ ዞን አስተዳደር ልዩ አማካሪ አቶ በርገኔ በቀለ አካባቢው በዘርፉ እምቅ አቅም ያለው በመሆኑ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ተናግረው እግር ኳስ ለማኅበረሰብ ውሕደትና ለሰላም ግንባታ ያለው ሚና ጉልህ በመሆኑ ሥልጠናው በዘርፉ ሊፈጠሩ የሚችሉ ተግዳሮቶችን የሚፈታ እንዲሁም የዘርፉን እድገትና የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የጋሞ ዞን ስፖርት መምሪያ ም/ኃላፊና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታመነ ተስፋዬ ሀገራችን የራስዋ የሆነ ስፖርታዊ እንቅስቃሴና ፍልስፍና እንዲኖራት ታዳጊዎችን ማሠልጠንና በዘመናዊ መንገድ ማብቃት እንደሚያስፈልግ አውስተው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ከማጠናከር ባሻገር ለሰብእና ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል ።

የዩኒቨርሲቲው ስፖርት አካዳሚ ዳይሬክተር አቶ አሰግድ ከተማ ዩኒቨርሲቲው ከክልሉ ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱን ጠቁመው የአሁኑ ሥልጠና መሠረት ያደረገው ታዳጊ ሕፃናት ላይ ነው ብለዋል፡፡ በእግር ኳስ ያደጉ ሀገራት ሕፃናት ላይ መሠረት አድርገው በመሥራታቸው ከፍተኛ ለውጥ ማምጣታቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ዩኒቨርሲቲው ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ተከትሎ ሳይንሳዊ ሥልጠናዎችን ከመስጠት አንፃር በምርምር የተደገፉ ሥራዎች እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች ከዚህ ቀደም በልምድ እያሠለጠኑ እንደቆዩ ተናግረው ሥልጠናው ዘመኑን ያገናዘበ እና በሳይንስና በጥናት የታገዘ በመሆኑ ተተኪ ትውልድ ለማፍራት የሚጠቅም ዕውቀት አግኝተናል ብለዋል፡፡ ልጆች ከልጅነታቸው የእግር ኳስ ዕውቀት እንዲኖራቸው፣ በየክለቦች የሚመለከቱትን ችግር ለመፍታትና የሀገራችንን የስፖርት ዘርፍ ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

በሥልጠናው መዝጊያ መርሃ ግብር ላይ የታዳጊ ሕፃናት የእግር ኳስ ፌስቲቫል የተካሄደ ሲሆን ለአሠልጣኞች ከጋሞ ዞን ስፖርት መምሪያ እና ከሠልጣኞች ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡

                                                                                                                                         የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት