በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ አዘጋጅነት ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አራት ወረዳዎች የመጡ የባሕል መድኃኒት አዋቂዎች፣ የግብርና ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች በተገኙበት ግንቦት 9/2016 ዓ/ም የግራንድ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ወርክሾፕ ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
ፕሮጀክቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሎኮዛ፣ ባስኬቶ፣ ዲራሼና ዳራማሎ ወረዳዎች የሚተገበር ሲሆን በማስጀመሪያ ወርክሾፑ ባሕላዊ መድኃኒቶች ተጠብቀው እንዲቆዩና ለትውልድ እንዲሻገሩ ለመድኃኒትነትና ለምግብነት የሚሆኑ ዕፅዋት የሚገኙባቸውን አካባቢዎች በሳይንሳዊ ምርምር በመታገዝ ጠብቆ ለማቆየትና ጫካዎች እንዳይመነጠሩ ለመከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በኮሌጁ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ ዕጩ ዶክተሮች የፕሮፖዛል ንድፈ ሃሳብ ቀርቧል፡፡ በዕጩ ዶ/ር አየለ ጫሽኬ የቀረበው ንድፈ ሃሳብ ‹‹Effect of Landscape Level Factors on Vascular Plants Diversity and Distribution, Forest Patch Dynamics and Ethnobotany in Melo Koza›› የሚል ርእስ ያለው ሲሆን ዕጩ ዶ/ር ብሩክ በዶሬ ‹‹Vascular Plant Diversity and Ethnobotany of Traditional Medicinal and Wild Edible Plants in Basketo Landscape, South Ethiopia›› በሚል ርእስ አቅርበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ በየአካባቢው የሚገኙ የባሕላዊ መድኃኒት ዕውቀቶችን ለመማማር፣ ለመሰነድና በዘላቂነት ለትውልድ ለማስቀጠል እየተደረገ ያለው ጥረት ሊበረታታ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የኮሌጁ የምርምር ዳይሬክተር ተወካይ አቶ እሳቱ በቀለ ከዕፅዋት የሚገኙ የባሕላዊ መድኃኒት ትሩፋቶች ለዘመናዊ መድኃኒት መሠረት በመሆናቸው በየአካባቢያችን የሚገኙ ዕፅዋትን መጠበቅና መንከባከብ ይገባል ብለዋል፡፡ አቶ እሳቱ ፕሮጀክቱ ለአካባቢያችን፣ አሁን ላለው አኗኗራችንና ለቀጣዩ ትውልድ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በኮሌጁ የብዝኃ ሕይወት ተመራማሪና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ትዕዛዙ ገብሬ በሀገራችን አብዛኛው ኅብረተሰብ ዕፅዋትን በባሕላዊ መንገድ ለመድኃኒትነት ከመጠቀሙና የዘመናዊ መድኃኒቶች ዋጋ ውድነት ለመግዛት የማያስችል ከመሆኑ አንጻር ፕሮጀክቱ ከባሕል መድኃኒት አዋቂዎች ጋር በጋራ ለመሥራት መጀመሩ የኅብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ትዕዛዙ ለመድኃኒትነት የሚሆኑ ባሕላዊ ዕፅዋትን ማጥናት፣ በዘላቂነት ለትውልድ እንዲቆዩ የማኅበረሰብ ተነሳሽነት መፍጠር፣ ከኅብረተሰቡ የተገኙ ዕውቀቶችን በዱር ውስጥ ከሚገኙት ዕፅዋት ጋር ማነጻጸር እንዲሁም ዕፅዋቱ የሚገኙባቸውን አካባቢዎችን ማጥናትና እንዲጠበቁ ማስቻል ፕሮጀክታቸው ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ከባስኬቶ ዞን ባካላ ቀበሌ የመጡት የባሕል መድኃኒት ዐዋቂ አቶ ግርማ ኃይሌ ከአባታቸው የተላለፈላቸውን የባሕል መድኃኒት ዕውቀት በመጠቀም ለማኅበረሰቡ እየሰጡ ያሉትን አገልግሎት እንዲያስቀጥሉ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስላበረታታቸውና በመድኃኒቶች ላይ ባላቸው ዕውቀት ዙሪያ አብሯቸው ለመሥራት በመፈለጉ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከመሎኮዛ ወረዳ የመጡት ሌላኛው የባሕል መድኃኒት ዐዋቂ አቶ ኑሩ ጉዳቶ ባሕላዊ መድኃኒቶችን ማሳደግና ማስፋት እንደሚገባ ገልጸው መድኃኒትነት ባላቸው ዕፅዋት ዙሪያ ከዚህ ቀደም ካላቸው ግንዛቤ ላይ ከዩኒቨርሲቲው መምህራን ተጨማሪ ዕውቀት በማግኘታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት