የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ልማት ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት በሥሩ ከሚገኙ አዲስና ነባር ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር ኅዳር 20/2017 ዓ/ም ውይይት ያካሄደ ሲሆን በዕለቱ የ2017 ዓ/ም ዕቅድ የውል ስምምነትም ከሥራ አስፈጻሚዎቹ ጋር ተፈራርሟል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ልማት ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን እንደገለጹት አዲሱ የሥራ አመራር ከነባሩ የሥራ አመራር ጋር ትውውቅ እንዲያደርግና የዩኒቨርሲቲውን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ አመራሩ የበኩሉን ሚና መወጣት በሚችልበት ሁኔታ ላይ የሥራ አመራር ለመስጠት ውይይቱ ተዘጋጅቷል፡፡ ወ/ሮ ታሪኳ አመራሩ የዩኒቨርሲቲውን ራእይና አሁናዊ የትኩረት አቅጣጫዎች በመገንዘብ በሥራ ላይ ብቻ በመጠመድ ለሌሎች መልካም ምሳሌ መሆን ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
የፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሣለኝ በበኩላቸው ሀገራዊና የዩኒቨርሲቲውን ለውጥ ተቀብሎ መራመድ የማይቀር ጉዳይ በመሆኑ አዳዲስ ሃሳቦችንና አሠራሮችን በመቀበል የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ያለውን ውስን ሀብት ቆጥቦ መጠቀም፣ ብክነትን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን መተግበር እንዲሁም የውስጥ ገቢ ምንጮችን በማሳደግ ሊሠራ እንደሚገባም ኃላፊዋ አስገንዝበዋል፡፡
የሚሠሩበትን ተቋም ራእይ ማወቅና ለሚገጥሙ ስጋቶች መፍትሔዎችን ማመላከት፣ ማቀድና ተግባራዊነቱን መከታተል፣ ራስን ማወቅና ብቁ ሆኖ መገኘት፣ ሙሉ አቅምንና ጊዜን በአግባቡ መጠቀም፣ ቆጥረው የተረከቡትን ሥራ ቆጥሮ ማስረከብ፣ አዳዲስ የቴክኖሎጂ አሠራሮችን መተግበር እንዲሁም የሠራተኞችን ብቃት በተለያዩ ሥልጠናዎች ማሻሻልና አስፈላጊ የሥራ ግብአቶችን ማሟላት የጥሩ መሪ ባህሪያት በመሆናቸው አመራሮቹ እነዚህን ባህሪያት እንዲከተሉ በመድረኩ አጽንዖት ተሰጥቶበታል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት