አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በ45 ዩኒቨርሲቲዎች ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት እና ከሥራና ክሂሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሀገራዊ የግብርና ናሙና ቆጠራ ለማካሄድ ከዞንና ወረዳዎች ለተወጣጡ ሠልጣኞች ከነሐሴ 17/2016 ዓ/ም ጀምሮ ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ተጠናቆ የሠልጣኞች ሽኝት መርሃ ግብር መስከረም 11/2017 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ በሥልጠናው ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተለያዩ ወረዳዎችና ዞኖች የተወጣጡ 858 ሠልጣኞች ተሳትፈዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ የተለያዩ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን ለማስፈጸም በዩኒቨርሲቲው በኩል በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰው ይህንንም ሥልጠና በዚሁ አግባብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ማስፈጸም መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ም/ፕሬዝደንቱ በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ በቂ ዕውቀትና ክሂሎት የሚጠይቅ ከመሆኑም ባሻገር ግልጸኝነት ያለውና የእውነተኛ መረጃ መርህን የተከተለ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ‹‹መሠልጠን ብቻውን ግብ አይደለም›› ያሉት ዶ/ር ዓለማየሁ ሀገራዊ ዕቅዶች የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖራቸው ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ወሳኝ ስለሆነ የሚሰበሰበው መረጃ እንደ ሀገር የምንመራበትን ዕቅድ ለማውጣት የሚረዳ፣ የሀገር መሪዎችና ተመራማሪዎች የሚጠቀሙበት እንዲሁም ትክክለኛ መረጃ እንዲኖራቸው የሚያግዝ በመሆኑ ሠልጣኞች ባገኙት ሥልጠና መሠረት በጥንቃቄ ትክክለኛና እውነተኛ መረጃ እንዲሰበስቡ በአጽንዖት አሳስበዋል፡፡
መሰል የቆጠራ ሥራ ከ22 ዓመታት በፊት መሠራቱን ያስታወሱት በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የአርባ ምንጭ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ስሜነህ አንበሴ ቆጠራ ለማካሄድ ከዞንና ወረዳዎች የተወጣጡ ሠልጣኞች ከሥልጠናው በኋላ ከሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ተግባራዊ በማድረግ የአገዳ፣ ቋሚና ጊዜያዊ ሰብሎችን የተመለከተ መረጃ ከአርሶ አደሩ በመሰብሰብ በታብሌት እንደሚመዘግቡ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ አስፈላጊ መረጃ የሚሰበስብ ሲሆን መረጃው ጂዲፒ/GDP/ ለመከለስ፣ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለተመራማሪዎች የሚረዳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እጅ ለእጅ ተያይዘን እያንዳንዷን እርምጃ በመራመድ በጋራና በመተጋገዝ በቂ መረጃ መሰብሰብ የሚችሉ ባለሙያዎችን ማፍራት ችለናል›› ያሉት ኃላፊው ለሥልጠናው ስኬታማነት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ላበረከተው አስተዋፅዖ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደግፌ አሰፋ በበኩላቸው የግብርና ናሙና ጥናት ሀገሪቷ ያለችበትን ሁኔታ የሚያሳይና የወደ ፊት አቅጣጫ የሚጠቁም በመሆኑ ሠልጣኞች በልዩ ጥንቃቄ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸው ኮሌጁ ለሥልጠናው ስኬታማነት ሠልጣኞችን በመቀበል ኦረንቴሽን የመስጠት፣ የምግብና የትራንስፖርት አገልግሎቶችን በማስተባበር የበኩሉን ሀገራዊ አስተዋጽዖ አበርክቷል ብለዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት