በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ 4ኛ ዓመት የሆርቲካልቸርና ዕፅዋት ሳይንስ ተማሪዎችና በኮሌጁ የማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ የተሠሩ የምርምር ሥራዎች የመስክ ምልከታ ሰኔ 24/2016 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ደግፌ አሰፋ በጉብኝቱ የተመለከቷቸው ሰብሎች የአካባቢውን አየር መላመድ፣ ድርቅንና በሽታን መቋቋም እንዲሁም በአጭር ጊዜ ውስጥ መድረስ እንዲችሉ ተደርገው የተሠሩ የምርምር ሥራዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ዲኑ የተጀመሩት ምርምሮች የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለመጨመር ብሎም የዩኒቨርሲቲውን ገቢ ማመንጫ አማራጭ ለማስፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡
በኮሌጁ የሆርቲካልቸር ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ አስጨናቂ ዳዊት በተማሪዎች ከሚሠሩ የመስክ ምርምር ሥራዎች በተጨማሪ እንደ ሙዝ፣ ሀባብ፣ ሽንኩርት፣ በቆሎና ሌሎችም በዩኒቨርሲቲው ድጋፍና ክትትል እየተከናወኑ ያሉ ሰብሎች እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡ እንደ መምህር አስጨናቂ የደረሱ አታክልትና ሰብሎችን ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የግቢው የማኅበረሰብ ክፍሎች በቅናሽ ዋጋ በማቅረብ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
ቲማቲም፣ ሀባብ፣ ቆስጣ፣ ቀይ ሽንኩርት፣ በቆሎ፣ ቃሪያ፣ ስኳር ድንች፣ ቦሎቄ፣ ሽንብራና አኩሪ አተር በኮሌጁ ተማሪዎች ምርምሮች እየተደረጉባቸው ከሚገኙ አዝርዕት፣ጥራጥሬና ሰብሎች መካከል ሲሆኑ ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን አጠናቀው ዩኒቨርሲቲውን ሲለቁ ምርምሮቹን ዩኒቨርሲቲው ተረክቦ ወደ ገቢ ማመንጫነት የሚቀየሩ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
በመስክ ጉብኝቱ የኮሌጁን ዲን ጨምሮ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ መምህራንና ተመራቂ ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት