በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት፣ በኢትዮጵያ የሕክምና ተማሪዎች ማኅበር እና በሮትራክት ክለብ አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ትብብር ለዩኒቨርሲቲው ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የዜሮ ፕላን አስተባባሪዎችና የክበባት ተጠሪ ሴት ተማሪዎች በጡት ካንሰርና በሥርዓተ ጾታ ዙሪያ ጥቅምት 29/2018 ዓ/ም ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ከፍተኛ ባለሙያ ወ/ሮ ማርእሸት ማቴዎስ ሥልጠናው በሥርዓተ ጾታ ምንነት፣ የአካላዊ ጥቃቶች ምንነት፣ መንስኤና ጾታዊ ጥቃቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ የሚወሰድ እርምጃና የማማከር አገልግሎትን አስመልክቶ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ ባለሙያዋ በሥልጠናው በአጠቃላይ ከሴት ተማሪዎች ጾታዊ ጥቃት ጋር ተያይዞ በሥራ ክፍላቸው የሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

በኮሌጁ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ ዓለማየሁ አሸናፊ ሥልጠናው በተለይ በሥርዓተ ጾታ ጉዳዮች ላይ ለሴት ተማሪዎች ግንዛቤን ለመፍጠርና በቀጣይ በጋራ ለመሥራት እንዲቻል በማለም የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ አስተባባሪው ጽ/ቤቱ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች አንዱ ዜሮ ፕላን ሲሆን ተማሪዎች በምን መልኩ መገልገል እንደሚችሉ በሥልጠናው ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች በመቻቻልና በመደጋገፍ እንዲማሩ እንዲሁም የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው እንዲጠናከር በመድረኩ መልእክት ተላልፏል ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ሕክምና ተማሪዎች ማኅበር አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ የመጡት አሠልጣኝ ዶ/ር ሮዳስ ዓለማየሁ በጡት ካንሰር ምንነት፣ በሚያመጣቸው ጉዳቶች፣ መከላከለያ መንገዶችና ሕክምናውን አስመልክቶ ግንዛቤ አስጨብጠዋል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት