አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት/Armauer Hansen Research Institute (Ahri) ጋር በመተባበር ‹‹AI Based Malaria Incidence Prediction under Current and Future Climate in South Ethiopia›› በሚል ርእስ ለሚሠራውና በሰው ሠራሽ አስተውሎት/Artificial Intelligence (AI) ላይ የተመሠረተ በአሁናዊና የወደፊት የአየረ ንብረት የወባ ክስተት ትንበያ የትብብር ፕሮጀክትን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር ጥቅምት 14/2018 ዓ/ም ምክክር አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል ዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰቡን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት በምርምር የተደገፈ መፍትሔ የማቅረብ ኃላፊነት የተጣለበት መሆኑን ተናግረው ባሉን በርካታ የልኅቀት ማእከላት ከተለያዩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር የምንሠራቸው ምርምሮች ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ ብለዋል፡፡ ከAhri ጋር በመተባበር የሚሠራው ይህ የወባ ምርምር አንድ ማሳያ ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሀገር የጀርባ አጥንት እንደመሆናቸው ፕሮጀክቱ በሀገራችን አሳሳቢ የጤና ችግር የሆነውን ወባ በሽታ በተመለከተ ዓለም በደረሰበት ቴክኖሎጂ ሳይንሳዊ ምርምር በማድረግ የበኩሉን ድርሻ የሚወጣበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው የምርምር ፕሮጀክቱ ለነባሩ የወባ ችግር ከዘመኑ ጋር የሚሄድና በቴክኖለጂ የተደገፈ መፍትሔ ለመስጠት የሚሠራ መሆኑንና የምክክር መድረኩም የፕሮጀክቱን አተገባበር በተመለከተ አዳዲስ ሃሳቦች የሚገኙበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወባ እና መሰል ተላላፊ በሽዎች ስርጭት ላይ የራሱ ተጽእኖ ያለው መሆኑን የጠቀሱተ ም/ፕሬዝደንቱ ይህንን ተጽዕኖ በዘመናዊ መልኩ መመዝገብና መከታተል በሽታውን በመከላከልና መቆጣጠር ሂደት ብሎም ሌሎች መሰል ጥናቶችን ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ የሚኖረው ነው ብለዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ቶማስ ቶሮራ የትብብር ፕሮጀክቱ ሐምሌ ወር 2016 ዓ/ም ይፋ መደረጉን አስታውሰው የፕሮጀክቱ ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ ለባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅ እንዲሁም በመረጃ አሰባሰብ ረገድ የገጠሙ ችግሮችና ቀጣይ ሂደቶች ላይ ለመወያየት የምክክር መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ቶማስ የተዘጋጁት የAI ሞዴሎች የሚገባላቸው መረጃ ትክክለኛና ግልጽ በሆነ መጠን የሚያቀርቡት ትንበያ ተአማኒነት የሚጨምር በመሆኑ በጤና ጣቢያ ደረጃ ተቋማዊ በሆነ መልኩ የተደራጀና ገላጭ መረጃ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም በምክክር መድረኩ የተገኙ የጤና አመራሮችና ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ዶ/ር ቶማስ ጠቁመዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ተመስገን መሐመድ በክልሉ ያለውን የወባ ክስተት አስመልክቶ ባቀረቡት ገለጻ እንደተመለከተው የወባ በሽታ በክልሉ አሳሳቢ የጤና ችግሮች ከሆኑት አንዱ ሲሆን ባለፉት 41 ሳምንታት ውስጥ ከተመረመሩ ሰዎች 38 ከመቶው ወባ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ምንም እንኳ ስርጭቱን ለመቀነስና ለመግታት በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ቢሆንም ይህ ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በ49.2 ከመቶ ጭማሪ ያሳየ ሆኗል፡፡
እንደ አቶ ተመስገን ከፍተኛ ተጋላጭነት ባላቸው ቦታዎች በመገኘት ድጋፍና ክትትል ማድረግ፣ የቅኝት ጥናት፣ ሕክምና፣ የግንዛቤ ማስጨበጥና አቅም ማጎልበትን ጨምሮ እንደ ክልል ብዙ ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም የአየር ጠባይ ለውጥና ሌሎችም ምክንያቶች የበሽታ ቁጥጥር ሥራውን አስቸጋሪ አድርገውታል፡፡ በዘንድሮው ዓመት በክልሉ የወባ ስርጭት ጋሞ ዞን ሰፊውን ድርሻ ሲይዝ ወላይታ፣ አሪ፣ ጎፋ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች በተከታታይ የተቀመጡ ሲሆን በእነዚህ አካባቢዎች በማተኮርና ሥራዎችን ተቋማዊ በማድረግ በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተቀናጅቶ የመሥራት ዕቅድ አለን ብለዋል፡፡ ለዚህም የምርምር ዩኒቨርሲቲ የሆነው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋነኛ አጋር በመሆን የጋራ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሮኒክ ትምህርት አስተዳደር ክፍል ዳይሬክተርና ከፕሮጀክቱ አባላት አንዱ የሆኑት ዶ/ር መሐመድ አበበ የፕሮጀክቱን ሂደት አስመልክቶ ባቀረቡት ገለጻ የወባ ክስተትን በተመለከተ እንደ ሀገር በትክክለኛ መረጃ ተመሥርቶ ቀድሞ መዘጋጀት ቢያስፈልግም ነባሩ የትንበያ ዘዴ በቂ አይደለም፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ሰው ሠራሽ አስተውሎት(AI)ን በመጠቀም የትንበያ ዘዴውን የበለጠ ለማዘመን ፕሮጀክቱን አስጀምሯል፡፡ አሁን ባለው ሂደት የአየር ጠባይና መሰል መረጃዎችን መሰብሰብ እና ሌሎችም ቅድመ ሁኔታዎች የተከናወኑ ሲሆን AI ሞዴሎቹ የወባ መረጃ አንዲሁም የወባ እና የአየር ጠባይ መረጃን በማጣመር በሁለት መልኩ የቀረበላቸውን መረጃ ተጠቅመው በጥሩ ሁኔታ ከትክክለኛው መረጃ ጋር ተቀራራቢ የሆነ ትንበያ ማስነበብ ችለዋል፡፡ ይህም በተመረጡ ቦታዎች ለመነሻ ያህል የተሠራ ሲሆን በቀጣይ ለየአካባቢው ተስማሚ የሆነውን ሞዴል በመምረጥ እና ግልጽና የተስተካከለ መረጃ ግብአት በማድረግ የተሻለ ትንበያ ለማግኘት እንዲሁም ሞዴሎቹን ወደ ዌብፔጅ የመቀየር ሥራ እንደሚሠራ ዶ/ር መሐመድ ጠቁመዋል፡፡
በምክክር መድረኩ የተገኙ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች አስፈላጊውን መረጃ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ አጠናቅረው ለማቅረብ እንዲሁም ለፕሮጀክቱ ስኬት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

