የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከደቡብ ኢትዮጵያ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ኢንተርኘራይዝ ጋር በመተባበር ሁለት የግድብና መስኖ አውታሮች ጥናትና ዲዛይን ሥራዎችን በማጠናቀቅ ከኅዳር 3-4/2017 ዓ.ም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የአዋጭነት ጥናት ሪፖርት ግምገማ አከናውኗል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ተመስገን ጥላሁን በሀገራችን ብሎም በክልላችን በርካታ በመስኖ የመልማት አቅም ያለው መሬት፣ የውኃ አማራጭ እና በቂ የሰው ሀብት ያለ ቢሆንም በዛው ልክ እንዳልተሠራ ገልጸው እንደ መንግሥት እና እንደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ያሉንን ፀጋዎች ለመጠቀም እንድንችል በጋራ አቅዶ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አቶ ተመስገን የሰገን እና የጨልቆ ግድብና መስኖ አውታሮች ጥናትና ዲዛይን ሥራ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ረዘም ያለ ግዜ መፍጀቱን አስታውሰው የአዋጭነት ጥናት ግምገማ ላይ የሚነሱ ገንቢ አስተያየቶችና ምክረ ሃሳቦችን በማካተት የጥናትና ዲዛይን ሥራዎቹን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ እንደ ም/ቢሮ ኃላፊው ተቋማቸው በቀጣይነት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ስነዶችን በማዘጋጀት ላይ ሲሆን በቀጣይ በመግባቢያ ሰነዱ መሠረት በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸውን የሰው ሀብትና ዕውቀት አስተባብሮ ክልሉን በመሰል ልማት ሥራዎች የመደገፍ ሥራ የሚሠራ ይሆናል፡፡
የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ቦጋለ ገብረማርያም ከደቡብ ኢትዮጵያ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ድርጅት ጋር በተደረገ ስምምነት የፕሮጀክት ሥራው መጀመሩን ገልጸው የመስኖ ልማትን ለማስፋት፣ የግብርና ምርትን ለማዘመን እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመስኖ አውታር ጥናቱ 1000 እና 8000 ሄክታር መሬቶችን ለማልማት መታቀዱን የገለጹት ዶ/ር ቦጋለ ጥናቶቹን ጨርሰን አስረክበን የምንተወው ሳይሆን እንደ መስክ ቤተ ሙከራ ለምርምርና ለመማር ማስተማር ግብዓት የምናውለው ነው ብለዋል፡፡ ከመማር ማስተማሩ ሥራ በተጨማሪ በልዩ ልዩ ኘሮጀክቶች የዩኒቨርሲቲውን መምህራን እና ተማሪዎች በማስተባበር በግድብ፣ በመስኖ እና በመጠጥ ውኃ የጥናትና ዲዛይን ሥራዎች ላይ ኢንስቲትዩቱ በስፋት እየተሳተፈ መሆኑንም ዶ/ር ቦጋለ ገልጸዋል፡፡
አክለውም የግድብና መስኖ አውታር ጥናትና ዲዛይን ሥራዎች ላይ የግድቡን ከፍታ፣ ውኃ የመያዝ አቅም፣ የሚለማው መሬት መጠን፣ የመስኖ አውታሮች ይዘት፣ የሚለሙ ዕፅዋትና አዝርዕት፣ የሚያስፈልጋቸው የውኃ መጠን መተንቢያ፣ የአፈር አጠባበቅ፣ የአካባቢ ተጽዕኖ መለየትና መከላከል፣ የካሳ ጥናት እንዲሁም ማኅበረሰባዊና እና ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት ጥናቶችን በማካተት ለእያንዳንዱ ኘሮጀክት ከ18 በላይ የጥናትና ዲዛይን ሥራዎች በመስክ እና በቢሮ ደረጃ ያሉ ጥልቅ መረጃዎችን በማሰባሰብ የጥናትና ዲዛይን ሥራዎቹን መከናወናቸውን ዶ/ር ቦጋለ ተናግረዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ መምህርና የሁለቱ ኘሮጀክቶች አስተባባሪ ዶ/ር ታምሩ ተሰሜ የኘሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን ሥራዎች ሦስት መሠረታዊ ሂደቶች የመጀመሪያው ዙር (Inception Report)፣ የአዋጭነት ጥናት (Feasibility Study Report) እና የመጨረሻ ጥናት (Detailed Design Report) እንዳላቸው አስታውሰው የጨልቆ ኘሮጀክት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን እንዲሁም የሰገን ኘሮጀክት በአዋጭነት ጥናት ደረጃ ላይ መሆኑን አስተባባሪው አመላክተዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ የፌዴራል እና የክልል ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት ሰፊ ዕቅድ መያዙን የገለጹት ዶ/ር ታምሩ ይህም ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ለመሆን የሚያደርገውን ጉዞ ከመደገፍ አንጻር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ታምሩ የጥናትና ዲዛይን ሥራዎቹ ተጠናቀው ወደ ሥራ ሲገባ የጨልቆ ኘሮጀክት በጎፋ ዞን እና ሰገን ደግሞ በቡርጂ እና ኮንሶ ዞኖች ላይ የሚሠራ ሲሆን የአካባቢውን ማኅበረሰብን በመስኖ ተጠቃሚ በማድረግ ሀገራችን የጀመረችውን ራስን በምግብ የመቻል እንቅስቃሴ በመደገፍ የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች በቀረበው የዳሰሳ ጥናት ላይ ግምገማ ያደረጉ ሲሆን በቀረቡ ዶክሜንቶች ላይ የታዩ ክፍተቶችን በመሙላት በሚሰጡ ገንቢ አስተያየቶችና ምክረ ሃሳቦች ዳብረው እና ተሻሽለው የጥናትና ዲዛይን ሥራዎቹ ወደ መሬት ወርደው መተግበር እንዲችሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት