የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ጥራትን፣ ፍትሃዊነትንና አግባብነትን ለማጠናከር ያለመ እና ባለፉት ዓመታት 12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና ምንም ተማሪ ባላሳለፉ ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት የሚያደርግ አዲስ አገራዊ የትብብር ፕሮግራምን በጋራ ለመፈጸም የሚያስችል ታሪካዊ የመግባቢያ ስምምነት (MoU) Imagine1day International Organization ጋር ዛሬ ግንቦት 21/2018 / በይፋ ተፈራርሟል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ይህ “Leaders in Teaching Ethiopia” (LiTE) የተሰኘው ፕሮግራም በትምህርት ሚኒስቴር እና በማስተርካርድ ፋውንዴሽን አጋርነት የሚደገፍ ሲሆን፣ Imagine1day መሪነት አንዲሁም በሌሎች አጋሮች ጋር በትብብር የሚተገበር መሆኑ ታውቋል።

ስምምነቱን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን በመወከል የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት / ተክሉ ወጋየሁ የፈረሙት ሲሆን፣ Imagine1day International በኩል ደግሞ የድርጅቱ ሪጂናል ማኔጀር አቶ አማኑኤል ኩሽቴ ፈርመውታል።

ስምምነቱ በአገር አቀፍ ደረጃ 12 ክልሎች እና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ በሚገኙ 700 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚተገበረውንና ከታህሳስ 2025 እስከ ህዳር 2030 የሚቆየውን LiTE ፕሮግራምን በጋራ ለመተግበር ያለመ ነው።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት / ተክሉ ወጋየሁ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ዩኒቨርሲቲው ይህንን ግዙፍ አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ያለውን ሙሉ ተቋማዊ ዝግጁነት ገልጸዋል። / ተክሉ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን ከማስፋፋት ባሻገር፣ ለአገራዊ የትምህርት ጥራት መሻሻል የሚጠበቅበትን ሚና ለመወጣት ምንጊዜም ቁርጠኛ መሆኑን አስገንዝበዋል። ይህ ፕሮጀክት ወቅታዊና በትምህርቱ ዘርፍ እንደ ሀገር የገጠመውን ስብራት ለመጠገን ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን በመጥቀስ፣ ትምህርት ላይ መስራት የመጪው ትውልድና የሀገር መጻኢ ዕድል የሚወስን በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ለመስኩ ሁለንተናዊ ለውጥ በትብብሩ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

Imagine1day International ሪጂናል ማኔጀር አቶ አማኑኤል ኩሽቴ በበኩላቸው፣ ይህ አገር አቀፍ ፕሮጀክት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ዘርፍ ላይ ዘላቂና መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የተወጠነ ታላቅ ተነሳሽነት መሆኑን ገልጸዋል። አቶ አማኑኤል የፕሮጀክቱ ዋነኛ ትኩረት የመምህራንን፣ የትምህርት ቤት አመራሮችንና የተማሪዎችን አቅም በከፍተኛ ደረጃ ማብቃት ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመው፣ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ የሥርዓተ-ጾታ እኩልነትንና አካቶ ትግበራን ማረጋገጥ፣ የሴት መምህራንን የአመራር ሚና ማሳደግ እንዲሁም የአካል ጉዳተኞችን ያካተተ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ምቹ የሥልጠና አካባቢን መፍጠር ቁልፍ ተግባራት መሆናቸውን አብራርተዋል። ለዚህም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ያለው ሰፊ ተቋማዊ አቅምና ሙያዊ ዝግጁነት ለፕሮግራሙ ስኬታማነት እንደ ጠንካራ የጀርባ አጥንት ሆኖ እንደሚያገለግል እምነታቸውን ገልጸዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥነ-ትምህርት እና ሥነ-ባህሪ ሳይንስ ትምህርት ቤት ዲን አቶ አንለይ ብርሃኑ በፕሮግራሙ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚታቀፉት 700 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 70 ያህሉ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ለክልሉ የትምህርት ጥራት መሻሻል ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል። አቶ አንለይ የፕሮጀክቱ ዋነኛ ትኩረት ባለፉት ዓመታት 12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና አንድም ተማሪ ማሳለፍ ያልቻሉ ትምህርት ቤቶች ላይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ይህ ትብብር የተማሪዎችን ውጤት በከፍተኛ ደረጃ ለማሻሻል በቁርጠኝነት እንደሚሠራና በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ቢያንስ 10 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አምጥተው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እንዲቀላቀሉ አቅዶ እንደሚንቀሳቀስ አስታውቀዋል። ለዚህም ስኬት /ቤቱ ከአዲሱ ብቃት-ተኮር ሥርዓተ-ትምህርት ጋር የተጣጣሙ የሙያ ማሻሻያ (CPD) ሞጁሎችን በጋራ በማዘጋጀት፣ መደበኛና የድብልቅ (blended) ሥልጠናዎችን ለሁለተኛ ደረጃ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል። በተጨማሪም በትምህርት አሰጣጥ ዙሪያ በተግባር ላይ ያተኮሩ ምርምሮችን በማካሄድና ምርጥ ተሞክሮዎችን በሰነድ በመያዝ፣ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚስተዋሉ ፈተናዎችን በሳይንሳዊ መንገድ ለመፍታት /ቤቱ ሙሉ አቅሙን አውጥቶ እንደሚሠራ ገልጸዋል።


አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የጥበብ ምንጭ!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት