አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ‹‹Koegu Language and Culture: Documentation, Description, and Dictionary Compilation›› የሚል ርእስ የተሰጠው በደቡብ ኦሞ ዞን የመጥፋት ስጋት የተጋረጠበትን የኮይጉ ቋንቋና ባህልን ለማጥናትና ለመሰነድ የሚያስችል የትብብር ፕሮጀክት ለመስራት ጥር 26/2017 ዓ/ም ስምምነት ተፈራርመው ፕሮጀክቱን በይፋ አስጀምረዋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ምርምር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የትብብር ፕሮጀክቶች መሥራትን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያበረታታ ገልጸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተገባው ስምምነት እንደ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ተብሎ የተጀመረውን የምርምር ፕሮጀክት ይበልጥ የሚያጠናክርና ሥራው በስፋት እንዲከናውን የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደ ሀገር ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ ያለው አንጋፋ ተቋም መሆኑን ያወሱት ዶ/ር ተስፋዬ ዛሬ የጀመርነው የትብብር ፕሮጀክት በሌሎች መስኮች ላይም ተባብረን እንድንሠራ እድል የሚከፍት ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ዳይሬክተር ዶ/ር ዮሐንስ  አድገህ በአብዛኛው ሀገረ በቀል በሆኑ ጉዳዮች፣ በሀገር ወስጥ ባሉ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ታሪኮች ዙሪያ ጥናቶችን ለማድረግ ዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት በእጀጉ አስቸጋሪ እንደመሆኑ በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ያለን የሰውና ውስን የገንዘብ ሀበት በጋር ለመጠቀም በመወሰን ፕሮጀክቱን በጋራ ለመስራት መወሰኑ ተገቢና ትክክለኛ  ነው ብለዋል፡፡  ይህ ፕሮጀክት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አነሳሽነት የተጀመረ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ዮሐንስ መሰል ምርምሮችን በማካሄድ የ53 ዓመታት ልምድ ያለው አካዳሚያቸው በፕሮጀክቱ የተሰጡትን ተግባራት በአግባቡ ለማከናወን ዝግጁና ቁርጠኛ መሆኑን አርጋግጠዋል፡፡ እንደ ኮይጉ ያሉ ጥቂት ተናጋሪ ያላቸውና በመጥፋት ስጋት ውስጥ ያሉ ባህሎችን፣ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን፣ ፍልስፋናዎችን ወዘተ ማጥናትና መሰነድ የሀገራዊ የምርምር ተቋማት ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት የሰጡት ዳይሬክተሩ በሌሎችም ተያያዥ መስኮች ተቋማቸው ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር የመስራት ፍላጎት ያለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪና ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ዳኘው ማቸ በደቡብ ኦሞ ኮይጉ ማኅበረሰብ የሚነገረው የኮይጉ ቋንቋ በአሁኑ ጊዜ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ተናጋሪዎች ያሉትና የመጥፋት ስጋት የተጋረጠበት እንደሆነና ይህንን በመገንዘብ ዩኒቨርሲቲው ቋንቋውንና ባህሉን የመሰነድ ሥራ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የኮይጉ ቋንቋና ባህልን በተለያዩ መንገዶች ሰንዶ ማስቀመጥና ለተውልድ ማስተላለፍ የትብብር ፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ዳኘው ከዚህም ባሻገር የቋንቋው ሰዋስዋዊ መገለጫ የሆኑት ድምጾች እና የቃላትና የዓረፍተ ነገር አወቃቀር ሥርዓት በስፋት ተጠንተውና ተሰንደው እንዲቀመጡ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በፕሮጀክቱ አራት ሺህ ቃላትን የያዘ የኮይጉ ቋንቋን በአማርኛና እንግሊዝኛ የሚተረጉም መዝገበ ቃላት የሚዘጋጅ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ዳኘው የማኅበረሰቡን ባህል፣ ሥነ ቃል፣ አኗኗርና ታሪክ የየመዝገብና የመሰነድ ሥራም ይሠራል ብለዋል፡፡

የትብብር ፕሮጀክቱ ለ3 ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 1.75 ሚሊየን ብር እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 1.5 ሚሊየን ብር የመደቡ መሆኑን እንዲሁም ከሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ 10 የዘርፉ ተመራማሪዎች በጥናቱ እንደሚሳተፉ ዶ/ር ዳኘው ገልጸዋል፡፡
በደቡብ ኦሞ ዞን የያንጋቶም ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ስንዲ አታቦ በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ትብብር የሚሠራው የትብብር ፕሮጀክት የማኅበረሰቡን ማንነት፣ ባህልና ሀገረሰባዊ ዕውቀቶች ከማቆየትና ሰንዶ ከማስቀመጥ አንጻር ጥልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረው እንደ አካባቢው ተወላጅም ሆነ እንደ ኃላፊ ለምርምሩ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት