የሀገራችን የብልጽግና እና የቁርጠኝነት ተምሳሌት በሆነው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ (GERD) ንጋት ሃይቅ ላይ ሲካሄድ የቆየው ዘመናዊ የውሃ ውስጥ የመሬት አቀማመጥ እና ጥልቀት ልኬት (Bathymetric Survey) የመጀመርያ ምዕራፍ መጠናቀቅን አስመልክቶ የተዘጋጀው የምህንድስና ካርታ የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ለኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን በይፋ አስረክቧል። በዚህ የርክክብ ስነ-ስርዓት ላይ የሁሉም ባለድርሻ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
ይህ ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክት የሀገርን አቅም ባስተሳሰረ መልኩ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ (በውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት) መሪነት፣ከኢትዮጵያ ባህር ኃይል፣ከኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን እና ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ በመተባበር በከፍተኛ የባለሙያዎች ጥን ካሬ የተከናወነ ስራ ነው።
በጠቅላላው 5 ምዕራፎችን ያቀፈው ይህ ግዙፍ የባዚሜትሪ ጥናት፣ አሁን ላይ እጅግ ፈታኝና ወሳኝ የሆነው የመጀመሪያው ምዕራፍ የውሃ ውስጥ ካርታ ስራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለባለድርሻ አካላት እንዲደርስ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም ቀሪዎቹን ምዕራፎች በተሻለ ፍጥነትና ጥራት ለማጠናቀቅ ትልቅ መተማመንን ፈጥሯል።
በሀገር በቀል ምሁራንና ተቋማት የዳበረው ይህ ካርታ ለግድቡ ዘላቂ አገልግሎትና ለሀገራዊ ኢኮኖሚው የሚኖረው ዘርፈ-ብዙ ፋይዳ ከፍተኛ ነው። ከእነዚህም መካከል በግድቡ ማጠራቀሚያ ሀይቅ ላይ ደህንነቱ የተጠበቀ የባህር ላይ ትራንስፖርት ለመዘርጋት እንዲሁም የቱሪዝም እና የውሃ ላይ መዝናኛዎችን በስፋት ለማስፋፋት ወሳኝ መመሪያ ሆኖ ያገለግላል።
በተጨማሪም የውሃውን ጥልቀትና ምቹ ስነ-ምህዳር በመለየት የዓሳ ሀብት ልማትን በዘመናዊ መልኩ ለማካሄድ የሚረዳ ከመሆኑም በላይ፣ የግድቡን ትክክለኛ የውሃ ይዘት (Volume) እና ጥልቀት (Depth) በትክክል ለማወቅና ወደ ግድቡ የሚገባውን የደለል ክምችት መጠን (Sediment Deposit) አስቀድሞ ለመገመትና መፍትሄ ለመስጠት ያገለግላል።
ይህ የተገኘው ሳይንሳዊ መረጃ እና የተዘጋጀው ካርታ ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር (MoWE) እንዲሁም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል (EEPCo) ግድቡን በብቃት ለማስተዳደር፣ የዕለት ተዕለት ስራዎችን ለመከታተልና ወቅታዊ የጥገና ስራዎችን (Operations and Maintenance) በምህንድስና የታገዘ ውሳኔ ለመስጠት ትልቅ ግብአት ነው።
ይህ ደማቅ ምዕራፍ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሀገራችን የውሃ ዘርፍ ያለውን እምቅ የምርምርና የቴክኖሎጂ አቅም በተግባር ያሳየበትና ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ደህንነትና አገልግሎት ማደግ ታሪካዊ አሻራውን ያሳረፈበት ነው።
እንኳን ደስ አለን!
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የጥበብ ምንጭ!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት


