በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለሚገኙ የተለያዩ አዳራሾች አገልግሎት የሚውል የአዳራሽ ወንበር ግዥ ሂደት ጋር ተያይዞ በተፈጠረ የጥራት/መስፈርት ልዩነት/ ችግር ምክንያት ከአቅራቢ ድርጅቱ ጋር መግባባት ባለመቻሉ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን ከዚህ ቀደም በተሰጡ መግለጫዎች ማሳወቃችን ይታወሳል፡፡ ጉዳዩን በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እና እንደ ኢሳትና ኢቲቪን በመሳሳሉ የግልና የመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጭምር የተዛቡና አሉባልታን መሠረት ያደረጉ ዘገባዎችና የዩኒቨርሲቲውን መልካም ስምና ዝና የሚያጎድፉ መረጃዎች ሲሰራጩ መቆየታቸውም ይታወቃል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
በጊዜው ‹‹43 ሚሊየን ብር ተዘርፏል›› እየተባለ በማኅበራዊ ሚዲያና በቴሌቪዥን ጣቢያዎች አጀንዳ ተደርጎ ሲሰራጩ የነበሩ መረጃዎች ትክክለኛ አለመሆናቸውን፣ ድርጅቱ ያቀረበው ወንበር በግዥ መስፈርቱ (specification) መሠረት ጥራቱን ጠብቆ አለመቅረቡ በመረጋገጡ ለድርጅቱ በቅድመ ክፍያ በሕጋዊ መንገድ ከተከፈለው ክፍያ ውጪ ምንም ዓይነት ክፍያ ያልተፈፀመ መሆኑ እንዲሁም ጉዳዩ በፍርድ ቤት ተይዞ በክርክር ላይ እንደሆነ ዩኒቨርሲቲው በሰጣቸው መግለጫዎች ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡
በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ማለትም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በድርጅቱ ቅሬታ አቅራቢነት እና ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በዩኒቨርሲቲው ቅሬታ አቅራቢነት ሲካሄድ የነበረው ክርክር የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ በመሆኑ ይህንን መግለጫ መስጠት አስፈልጓል፡፡
በውሳኔውም ድርጅቱ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት ወንበሩን አለማቅረቡ ለክርክሩ መንስኤ መሆኑ በፍርድ ቤቶቹ በመረጋገጡ ድርጅቱ ላጎደለው ጥራት ከተስማማው ገንዘብ ላይ ተቀናሽ ተደርጎ ወንበሩን ገጥሞ ሲያጠናቅቅ ክፍያውን እንዲቀበል ተወስኗል፡፡ በፍርድ ቤት የአሠራር ሂደት ጉዳዩ የዘገየ ቢሆንም ውሳኔው በዩኒቨርሲቲው አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ በዚህም መሠረት የወንበር ገጠማው በአዳራሾቹ እየተከናወነ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
የወንበር ግዥው ጉዳይ የፍርድ ቤት ውሳኔ ከግዥው ጋር ተያይዞ ሲደረጉ የነበሩ አሉታዊ የሚዲያ ዘመቻዎችን ራቁት ያስቀረ እንዲሁም የግልም ሆነ የመንግሥት ሚዲያዎች ለሕዝብ ተደራሽ የሚያደርጉትን መረጃ በጥንቃቄ ማጣራት እንደሚገባቸው ያረጋገጠ ነው፡፡
በመጨረሻም ከዚህ የወንበር ግዥ ሂደት ጋር ተያይዞ እውነታን ሆን ብሎ በመደበቅ የራሳቸውን እኩይ ዓላማ ለማሳካት ሲሞክሩ የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦችና ተቋማት በዩኒቨርሲቲው የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት እንደተመዘበረና እንደተዘረፈ በማስመሰል የሚዲያ ሥነ ምግባርን በጣሰ መልኩ የተዛቡ ዘገባዎችንና መረጃዎችን ሲያሰራጩ የነበሩ ማኅበራዊ ሚዲያዎችና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እውነታው ይህ መሆኑን ተገንዝበው ዩኒቨርሲቲውን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁና በተሳሳተ ሁኔታ ያሠራጯቸውን ዘገባዎች፣ ዶክሜንተሪዎችና መረጃዎች ከማኅበራዊ ሚዲያዎቻቸው፣ ከዩቲዩብና ሌሎች የሚዲያ ፕላትፎርሞች ላይ እንዲያነሱና ማስተካከያ እንዲያደርጉ ዩኒቨርሲቲው በጥብቅ እየጠየቀ በዚህ ሂደት ውስጥ ከዩኒቨርሲቲው ጎን ለነበራችሁ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ፣ የቀድሞ ምሩቃን እንዲሁም በፍርድ ሂደት ውስጥ ያለመሰላቸት ሙያዊ ኃላፊነታችሁን በመወጣት ክርክሩ ፍትሕን እንዲሁም የዩኒቨርሲቲውን ብሎም የመንግሥትና የሕዝብ ጥቅም ባረጋገጠ መልኩ እንዲጠናቀቅ ላደረጋችሁ በሁሉም ደረጃ ላላችሁ የፍትሕ አካላትና ለዩኒቨርሲቲው ሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ኃላፊና ባለሙያዎች ዩኒቨርሲቲው ምስጋና ያቀርባል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት