አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከጋሞ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ጋር በመተባበር ለነባር አሽከርካሪዎች በአሽከርካሪዎች ሥነ ባህርይ፣ የተሸከርካሪዎች ቴክኒክና የትራንስፖርት ሕግና ደንብን አስመልክቶ ኅዳር 17/2015 ዓ/ም የማነቃቂያ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ነገን ለመኖር  ዛሬን ተጠንቅቆ ማሽከርከር ይገባል ያሉት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ አሽከርካሪዎች የመሰል ሥልጠናዎችን ግብዓት እንደ ስንቅ በመያዝ፣ እርስ በርስ በመማማርና ከራስ ልምድም ጭምር የግለሰብ አቅምን በማሻሻል የዩኒቨርሲቲውን ንብረት በጥንቃቄና በኃላፊነት መያዝና የትራፊክ ሕግና ደንብን በማክበር በመልካም ሥነ-ምግባር ማኅበረሰቡን ማገልገል  እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ጠቅላላ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ወልዴ እንደገለጹት ሥልጠናው ማኅበረሰቡ ከዘርፉ የሚያገኘው አገልግሎት የተሻለ እንዲሆን በአገልግሎት ሰጪዎች በኩል የሚታዩትን ክፍተቶች በመሙላት ከአደጋ የጸዳና በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፀ ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም የተቋሙን አፈጻጸም ለማሳደግ የአሽከርካሪዎችን የቴክኒክ ክሂሎት በማጎልበት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲላመዱ ለማድረግ ታስቦ ነው ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ጌታቸው አትሞ ባለፉት ዓመታት በአጠቃላይ በዞኑ ሲከሰቱ የነበሩ አደጋዎች ለመፈጠራቸው በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋነኛ መንስኤው የአሽከርካሪዎች ጥንቃቄ ጉድለት በመሆኑ አሽከርካሪዎች ከሥልጠናው ግንዛቤ አግኝተው  የባህርይ ለውጥ እንዲያመጡና አደጋን የሚከላከል ብቃት ያለው አሽከርካሪ እንዲሆኑ ታልሞ የተዘጋጀ ሥልጠና መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ለተገልጋይ አክብሮትና ጥሩ ስነ-ምግባር ያለው፣ ንብረትን የሚጠብቅና ኃላፊነት የሚሰማው እንዲሁም የሰውን ሕይወት የሚታደግ አሽከርካሪ በመፍጠር በቀጣይ ጊዜያት አደጋን ለመቀነስ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡ 

የጋሞ ዞን የትራፊክ ሰልፍ ቁጥጥር ማስተባበሪያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ደሳለኝ ሸዋንድራስ እንደገለጹት አሽከርካሪዎች ከሱስ የጸዱ፣ ጥሩ ስነ-ምግባር ያላቸው፣ አደጋን በመከላከል ራሳቸውንም ሆነ ኅብረተሰቡን ለመጠበቅ ቁርጠኛ  ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡  

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሰው ሀብትና ልማት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይና የዳይሬክቶሬቱ  የትምህርትና ሥልጠና ቡድን መሪ ሻለቃ አበበ አማረ በበኩላቸው የጠቅላላ አገልግሎት ክፍል በርካታ የሰው ሀይል ያለበት ከመሆኑም በላይ የተለያዩ ተገልጋዮችን የሚያስተናግድና ትኩረትን የሚሻ ዘርፍ በመሆኑ ለባለሙያዎቹ የተለያዩ የማነቃቂያ ሥልጠናዎች ሊሠጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ 

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው በጣም አስፈላጊና ራሳቸውን በዕውቀትና በክሂሎት እንዲያጎለብቱ፣ ለሕግ እንዲገዙና የአገልጋይነት መንፈስን እንዲላበሱ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡  

በመጨረሻም በሥልጠናው ላይ በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት የተደረገ ሲሆን ለሠልጣኞችም የተሳትፎ ምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት