ዩኒቨርሲቲው ከጋሞ ቴሌቪዥን ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የሁለትዮሽ ስምምነት መግባቢያ ሰነድ ጥር 06/2017 ዓ/ም ተፈራርሟል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ትብብር ተ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ቀደም ሲል በዞኑ መሰል የሚዲያ ተቋማት ባለመኖራቸው የዩኒቨርሲቲው ሥራዎች በሚፈለገው ልክ ለማኅበረሰቡ አለመድረሳቸውን ጠቅሰው ይህም ኅብረተሰቡ ዩኒቨርሲቲ ስለሚያከናውናቸው ዘርፉ ብዙ ተግባራት በቂ መረጃ እንዳይኖረው አድርጓል ብለዋል፡፡ ዛሬ በተፈረመው ስምምነት መሠረት በዩኒቨርሲቲው የሚሠሩ የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎች ብሎም ወደ ማኅበረሰቡ የተሸጋገሩ ቴክኖሎጂዎችና ሌሎችም ወሳኝ ሥራዎችን አስመልክቶ ጋሞ ቴሌቪዥን መረጃዎችን በተለያየ መልኩ ተደራሽ የሚያደርግ መሆኑን ዶ/ር ተክሉ ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አዲሱ አዳሙ በበኩላቸው ከአንጋፋው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር ለመሥራት ስምምነት መፈራረማችን ትልቅ ዕድል በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ ሥራ አስኪያጁ በስምምነቱ መሠረት ድርጀታቸው ዩኒቨርሲቲው ለሚሠራቸው ሥራዎች የሚዲያ ሽፋን እንደሚሰጥ ገልጸው ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ በሰው ኃይል፣ በዕውቀት፣ በምርምርና ሥልጠና እንዲሁም በቁሳቁስ ድርጅቱን በመደገፍ በጋራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ ይህም በጋሞ ቴሌቪዥን እና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መካከል ስትራቲጂክ አጋርነት በመመሥረት የዩኒቨርሲቲውን ሥራዎች በቅርበትና በተደራጀ መልኩ ለማስተዋወቅ እንዲሁም ጋሞ ቴሌቪዥን ሀገራዊ ትኩረት የሚያገኙ ይዘቶች ምንጭ እንዲሆን የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ 

የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ሥራዎችን በመለየት በጋራ ማቀድና ማጽደቅ፣ የትብብር ሥራዎችን ይዘት መወሰንና መምራት፣ የሚፈጸሙ ተግባራትን ክትትል ማድረግ፣ የፕሮግራም ይዘቶችን በሚመለከታቸው ባለሙያዎችና ኃላፊዎች አስገምግሞ ማጽደቅ፣ ለትብብር ሥራው የሚያስፈልጉ ወጪዎችን መመደብ እንዲሁም ለቴሌቪዥን ድርጅቱ የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ የዩኒቨርሲቲው ዋና ዋና ተግባርና ኃላፊነቶች መሆናቸው በመግባያ ሰነዱ ተመልክቷል፡፡

በጋሞ ቴሌቪዥን በኩል የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ሥራዎችን ማቀድ፣ የድርጊት መርሃ ግብር ማውጣት እና የሚያስተባብሩና የሚያስፈጽሙ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችን የመመደብ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም፣ ዘጋቢ ፊልም፣ ፕሮሞሽናል ክሊፕ፣ ማስታወቂያ፣ ቀጥታ ስርጭት፣ የፓናል ውይይት እና መሰል ፕሮዳክሽኖችን በራሱ ባለሙያዎች የማከናወንና የማቅረብ ተግባርና ኃላፊነቶች አሉት፡፡

የመግባቢያ ሰነዱ የአንድ ዓመት የትግበራ ጊዜ ያለው ሲሆን በሰነዱ መሠረት ዩኒቨርሲቲው የሥራ ትእዛዝ ሲሰጥና ተናጠል ውሎች ተዘጋጅተው ሲፈረሙ ሥራዎቹ ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡


አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት