በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ፣ አፈጻጸምና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ትናንት ነሐሴ 7/2018 ዓ.ም ሰፊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል። በመድረኩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንትና ምክትል ፕሬዝደንቶች፣ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና የሆስፒታሉ የሥራ ኃላፊዎች፣ ሐኪሞች፣ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም የአስተዳደር ሠራተኞች ተሳትፈዋል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፤ የሆስፒታሉን አሰራር ማጠናከርና ማደራጀት የዩኒቨርሲቲው አመራር ቅድሚያ የሚሰጠው ዋና ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም ከፍተኛ አመራሩ ሆስፒታሉ በሚፈለገው ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጥ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ የኦክስጂን ፕላንት ግንባታና ተከላ ተጠናቆ ሥራ ይጀምራል ብለዋል። በተጨማሪም ባለፈው ዓመት የተኝቶ ሕክምና አገልግሎት እንዲጀምር ከፍተኛ ጥረት መደረጉን አንስተው፣ በቀጣይም የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማስፋት፣ ጥራታቸውን ለመጠበቅና በቁሳቁስ እንዲሁም በግብአት ለማሟላት አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንትና የሆስፒታሉ ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በቀጣይ በትኩረት ሊሰሩ የሚገባቸውን ዋና ዋና አቅጣጫዎች አመላክተዋል። የሕንጻውን ቀሪ ሥራዎች በአስቸኳይ ማጠናቀቅና እስካሁን ያልተጀመሩ የአገልግሎት ዘርፎችን ማስጀመር እንደሚገባ ገልጸዋል። የሆስፒታሉን አገልግሎቶች ከዩኒቨርሲቲው ዋና ዋና የትኩረት መስኮችና ተልዕኮዎች ጋር ማገናኘት፣ በቂ የሰው ኃይልና ግብአት በማሟላት መስክ ለይቶ የስፔሻሊስት ትምህርቶችን ማስጀመር፣ እንዲሁም ሆስፒታሉ በራሱ ትልቅ የምርምር ማዕከል በመሆኑ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጎን ለጎን ለችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎች ከፍተኛ ትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል። በተጨማሪም ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ ጉዳዮች ላይ ማተኮርና አጣዳፊ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመለየት መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ዶ/ር ተክሉ ለሆስፒታሉ እድገትና ስኬት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ላሳዩት ቁርጠኝነት፣ ልዩ ትኩረትና በየጊዜው ላደረጉት የቅርብ ክትትል የላቀ ምስጋና አቅርበው ለሆስፒታሉ አመራሮችና ሙሉ የሥራ ባልደረቦች ላበረከቱት አስተዋጽኦና ላሳዩት ትጋት ላቅ ያለ ምስጋናቸውን ችረዋል።
የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ቦጋለ ገብረማርያም ሆስፒታሉ እስካሁን ያሳየው የእድገትና የአገልግሎት አሰጣጥ እንቅስቃሴ የሚያረካ መሆኑን ገልጸው፤ ነገር ግን በቀጣይ በርካታ ሥራዎች እንደሚጠበቁ ጠቁመዋል። በተለይም ለተማሪዎች የመማር ማስተማር ሥራ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ለማሟላት ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ጳውሎስ ታደሰ በሆስፒታሉ የተመለከቱትን የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የእድገት እንቅስቃሴና የፅዳት ደረጃ አደንቀዋል። ፕሮፌሰር ጳውሎስ አክለውም ከግዢ ሂደት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።
የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ በበኩላቸው፣ ሆስፒታሉ የሚጠበቅበትን አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል። አክለውም ከመንግሥት በጀት በተጨማሪ አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ዘርፎች የበለጠ ለማስፋት ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከግለሰቦችና ከዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪዎች (አሉምናይ) ድጋፍ ለማግኘት ሰፊ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል። ዶ/ር ደስታ አያይዘውም፣ ማህበረሰቡ አገልግሎት በጀመረባቸው ዘርፎች በማስተማሪያና ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ የሪፈራል ወረቀት መያዝ ሳያስፈልገው የ24 ሰዓት ሙሉ አገልግሎት ማግኘት የሚችል መሆኑንም ገልጸዋል።
በሆስፒታሉ የጤና ትምህርትና ሕክምና አገልግሎት ኮርፖሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ብርሃኑ አንዳርጌ ለውይይት መነሻ የሚሆን ዝርዝር ገለጻ በእለቱ አቅርበዋል። ዶ/ር ብርሃኑ በገለጻቸው፣ ሆስፒታሉ በተመላላሽ ሕክምናና በተለያዩ የምርመራ መስኮች አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ዕለት አንስቶ የአገልግሎት አድማሱን እያሰፋ መምጣቱን ገልጸው፣ የሥራ እንቅስቃሴዎችን፣ አፈጻጸሞችን፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንና መልካም አጋጣሚዎችን በዝርዝር አብራርተዋል።
በዕለቱ የቀረበውን ገለጻ ተከተሎ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው በተቋሙ አመራሮች ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን በቀጣይ ለሆስፒታሉ ዕድገት በጋራና በትብብር ለመስራት መግባባት ላይ በመድረስ ውይይቱ ፍጻሜውን አግኝቷል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የጥበብ ምንጭ /Spring of Wisdom
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

