የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል አባላት፣ የፌዴራል ፖሊስ አባላት፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና ተማሪዎች በተገኙበት በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ላንቴ ቀበሌ በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኞች ለመትከል የተያዘው ሀገራዊ መርሃ ግብር አካል የሆነ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ነሐሴ 17/2016 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአረንጓዴ አሻራ ጥሪ ተከትሎ በርካታ ችግኞችን በዩኒቨርሲቲው ግቢዎች፣ በአርባ ምንጭ ከተማና ዙሪያ አካባቢዎች ላይ በተከታታይ የችግኝ ተከላ ሲከናወን የቆየ ሲሆን ይህም በአየር ለውጥና ውበት ላይ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ እንደ ዩኒቨርሲቲም ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶበት በዓመታዊ ዕቅድ ተይዞ የተተከሉ ችግኞችን በተለየ መልኩ እንክብካቤ እየተደረገ በመሆኑ ከዚህ ቀደም የተተከሉ ችግኞች ጸድቀው ለአካባቢው አየር ሁኔታ መሻሻል፣ ለከተማው ውበት፣ ለአፈር ጥበቃና ለተራቆተው ደን ማንሰራራት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ፕሬዝደንቱ ጠቁመዋል፡፡ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የአንድ ቀን ብቻ ተግባር ሳይሆን በቀጣይነት የሚሠራ ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲው በዘጠኝ የችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች በቋሚነት ሠራተኛ መድቦ ችግኝ በማፍላት እንደየአካባቢው ሁኔታ ለምግብነት፣ ለአካባቢ ውበትና ለአፈር ጥበቃ አገልግሎት የተዘጋጁ ችግኞችን ለማኅበረሰቡ እንደሚያሰራጭም ዶ/ር ዳምጠው ገልጸዋል፡፡ የዘንድሮው አየር ሁኔታ የክረምቱ ዝናብ በበቂ ሁኔታ እየዘነበ የሚገኝ ስለሆነ ይህም ለችግኝ ተከላ ሥራ ተስማሚና ትልቅ ዕድልም ስለሚሆን ማኅበረሰቡ ችግኝ በመትከል አካባቢውን አረንጓዴ ከማድረግ ባለፈ የአፈር መሸርሸርን ለመካለከል እንደመፍትሄ እንዲጠቀም እንዲሁም እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋምም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት በሁሉም ካምፓሶችና ሌሎች በተመረጡ ቦታዎች የችግኝ ተከላው በቀጣይነት እንዲሠራ ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ የልማት ሥራዎች አስተባባሪ አቶ ደፋሩ ደበበ እንደገለጹት የዛሬው ችግኝ ተከላ ሀገራዊ ጥሪን ተከትሎ የተፈጸመ መሆኑን ገልጸው በ2016 ዓ/ም በተከታታይ በተለያዩ ጊዜያት በካምፓሶች የተተከሉትን ጨምሮ 2,500 የቆላ ቀርቀሃ፣ ቡና፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ወይበታና ሌሎች ሀገር በቀልና የውጪ ችግኞች መተከላቸውን አቶ ደፋሩ ገልጸዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት