የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያ እና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የምረቃ ሂደት በስኬት እንዲጠናቀቅና ሥራ እንዲጀምር ላደረጉ አካላት የምስጋናና ዕውቅና ሥነ ሥርዓት መስከረም 25/2017 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ


በዕለቱ የሆስፒታሉን ምረቃ በገንዘብና በዓይነት ስፖንሰር ላደረጉ ባለሀብቶችና ድርጅቶች፣ በተለያዩ ኮሚቴዎች ሥር ሆነው በአመራርነትና በአባልነት ላገለገሉ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞችና ባለድርሻ አካላት የምስጋና እና ዕውቅና የምሥክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን ለሆስፒታሉ ምረቃና ሥራ መጀመር ለተጫወቱት ከፍተኛ የአመራርነት ሚና ልዩ ምስጋና ከፕሮግራሙ ታዳሚዎች እና ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ተችሯቸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የሆስፒታሉ መመረቅና ሥራ መጀመር የዩኒቨርሲቲውን ደረጃ ከፍ የሚያደርግና ለአካባቢው እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር ዳምጠው የሆስፒታሉ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ባማረ መንገድ እንዲጠናቀቅና የግንባታ ሥራው በታቀደው ልክ እንዲሄድ ላደረጉት ለግንባታው ተቋራጭ እና አማካሪ ድርጅት እንዲሁም ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ ለጤና ሚኒስቴርና ገንዘብ ሚኒስቴር ላሳዩት ትብብር በዩኒቨርሲቲው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አመራሮችና መምህራን እንዲሁም ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች በወቅቱ ያሳዩት የሥራ ትጋትና ቁርጠኝነት የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ባማረ ሁኔታ እንዲጠናቀቅና ሥራ እንዲጀምር ሚና ጉልህ የነበረው መሆኑን ዶክተር ዳምጠው አክለዋል::

የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጥያቄ መሠረት በማድረግ በተለይ ከ2014 ዓ/ም ጀምሮ ከግንባታ ባሻገር ሆስፒታሉን በግብዓት ለማሟላት ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ለሆስፒታሉ ሥራ መጀመር በርካታ አካላት የበኩላቸውን ተወጥተዋል ያሉት ወ/ሮ ታሪኳ 10 ኮንቴይነር የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገው ሂዩማን ብሪጅ እና የድርጅቱን የሀገር ውስጥ ዳይሬክተር ዶ/ር አዳሙ አንለይ ውለታ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና መቼም የማይዘነጋ ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የግንባታ ተቋራጩና አማካሪ ድርጅቱ ላሳዩት ቁርጠኝነት፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የግዥና ንብረት ባለሥልጣን፣ ጋሞ ዞን፣ የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደርና ነዋሪዎች እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ለሆስፒታሉ እዚህ ደረጃ መድረስ እንዲሁም የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በጥሩ ሁኔታ እንዲካሄድ ትልቅ ሚና የተወጡ በመሆናቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ ሆስፒታሉ ከግንባታ ሥራ አንስቶ ሥራ እስኪጀምር ድረስ የበኩላቸውን ሲወጡ ለቆዩ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎችና ለዩኒቨርሲቲው ማኀበረሰብ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ቁርጠኝነትና ትጋት እንዲሁም የመላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ትብብር ለሆስፒታሉ ሥራ መጀመር የጎላ ሚና እንደነበረውም ዶ/ር ደስታ አክለዋል፡፡

የጤና ትምህርትና ሕክምና አገልግሎት ኮርፖሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ብርሃኑ አንዳርጌ የሆስፒታሉን አሁናዊ ሆኔታ በተመለከተ ባቀረቡት አጭር ገለጻ ሆስፒታሉ ሐምሌ 9/2016 ዓ.ም በይፋ ሥራ መጀመሩን አስታውሰው እስከ አሁን ከ390 በላይ ታካሚዎች የኤም አር አይ፣ 430 ታካሚዎች የሲቲ ስካን፣ 650 የአካባቢው ነዋሪዎች የተመላላሽ ሕክምና እንዲሁም 540 የሚያህሉ ደግሞ የተለያዩ የላቦራቶሪ አገልግሎቶችን ማግኘታቸውን ዶ/ር ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያ እና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ተመርቆ አገልግሎት መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት