በ‹‹AMU-IUC›› ፕሮግራም 4ኛው ፕሮጀክት በሲሌ እና ሻፌ ንዑስ ተፋሰሶች ላይ የአፈር መሸርሸርን በተመለከተ እየተከናወኑ ባሉ የምርምር ሥራዎች ዙሪያ በፕሮጀክቱ 2ኛ ዙር የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች ባሉበት ጥር 5/2015 ዓ/ም ሰሚናር አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ምስሎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
በ‹‹AMU-IUC›› ፕሮግራም የፕሮጀክት IV አስተባባሪ ዶ/ር ቶማስ ቶሮራ እንደገለጹት በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ዙር ሥራ ሦስት የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች በቤልጂየም እና ሁለት የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ተደርጎ በምርምሮቻቸውም በአካባቢዎቹ የአፈር መሸርሸር ችግርን የመለየት ሥራ እንዲያጠኑ ተደርጓል፡፡ እንደ አስተባባሪው በ2ኛ ዙር ፕሮጀክቱ የሚያተኩረው በመጀመሪያው ዙር የተለዩ ችግሮችን በመከላከልና መፍትሄ በማምጣት ላይ ነው፡፡ በፕሮጀክቱ የሚማሩ ተማሪዎች በትምህርትና ምርምራቸውን በሚሠሩበት ጊዜ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የምርምር ውጤቶች ወደማኅበረሰቡ እንዲደርሱ በትኩረት እንደሚሠራም አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡
በፕሮጀክቱ በመጀመሪያ ዙር የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ዕድል አግኝተው ከነበሩትና በዕለቱ የምርምር ሥራዎቻቸውን ካቀረቡት አማካሪዎች መካከል የውሃ ሀብትና መስኖ ምኅንድስና ፋከልቲ መምህር የሆኑት ዕጩ ዶ/ር ዓለማየሁ ካሣዬ የሸፌና ኤልጎ ንዑስ ተፋሰሶች ላይ ባደረጉት ምርምር መሠረት ከኤልጎ ወንዝ ከፍተኛ የሆነ አፈር ወደ ጫሞ ሐይቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በመርሃ-ግብሩ በፕሮጀክቱ 2ኛ ዙር የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ዕድል ላገኙ ተማሪዎች ከቤልጂየም የተመደቡ የምርምር አማካሪዎች የ3ኛ ዲግሪ የምርምር ሥራዎቻቸውን አቅርበው ውይይት ተካሂዷል፡፡
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት