የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማእከል ሥራዎቹን በተጠናከረና ስልታዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን የካቲት 6/2018 ዓ/ም ስትራቴጂክ አማካሪ ቡድን አቋቁሟል። በዕለቱ የማእከሉ የቀጣይ አምስት ዓመታት የተከለሰ ስትራቴጂክ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በ"Task force for Global Health" ዓለም አቀፍ ድርጅት የአፍሪካ ሪጅን ዳይሬክተር እና ከማእከሉ መሥራቾች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ተሾመ ገብሬ የማእከሉን ምሥረታ ሲያስታውሱ ማእከሉ እ.ኤ.አ በ2015 ሲቋቋም በወቅቱ በበሽታዎቹ ዙሪያ የሚሠራ ራሱን የቻለ ተቋም አለመኖሩን ታሳቢ በማድረግና የጤና ሚኒስቴር የሚሠራቸውን ፕሮግራሞች በምርምርና በሥልጠና ለመደገፍ ታልሞ መቋቋሙን ይናገራሉ።

እንደ ዶ/ር ተሾመ በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ በርካታ አጋሮችን ማፍራት የቻለው ማእከሉ በዐሥር ዓመታት ጉዞው  በምርምር፣ በሥልጠና እና በመሥክ ሥራ ቁጥጥርና ግምገማ ሥራዎች ለተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ቁጥጥር ከፍተኛ አስተዋጾኦ አበርክቷል። 

አሁን ላይ የተቋቋመው አማካሪ ቡድንም ከተለያዩ የትምህርትና ምርምር ተቋማት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተመረጡ ከፍተኛ ባለሙያዎችን ያካተተ ሲሆን በቴክኒካዊ ጉዳዮች፣ በሀብት አጠቃቀምና ሌሎችም ስትራቴጂያዊ ምክሮችን በመስጠት፣ አቅጣጫ በማመላከት፣ የምርምር ርእሶችን በመምረጥ እንዲሁም ከተለያዩ የምርምርና የትምህርት ተቋማት ጋር ግንኙነቶችን በመፍጠር የማእከሉን ሥራዎች ይበልጥ የሚያጠናክርና ስኬታማ የሚያደርግ መሆኑን ዶ/ር ተሾመ ገልጸዋል።

በመድረኩ ቀጣይ የአማካሪ ቡድኑ ሥራዎች፣ የትኩረት አቅጣጫዎች፣ የውይይት ጊዜያት እና ሌሎችም ለማእከሉ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች ተነሥተው ውይይት የተካሄደ ሲሆን በአመራር ረገድ የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት (Ahri) ዋና ዳይሬክተር ፕ/ር አፈወርቅ ካሱ በሊቀመንበርነት፣ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በም/ሊቀመንበርነት እና የማእከሉ ዳይሬክተር ረ/ፕ አብነት ገ/መስቀል በጸሐፊነት አማካሪ ቡድኑን እንዲመሩ ተመርጠዋል።

የማእከሉ ዳይሬክተር ረ/ፕ አብነት ገ/መስቀል ማእከሉ ባለፉት ዐሥር ዓመታት ባከናወናቸው  መጠነ ሰፊ ሥራዎች በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነትና ተአማኒነት ማትረፉን ገልጸው ማእከሉ የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎችን አስመልክቶ ወቅቱን የዋጀ  ዕቅድና ትግበራ እንዲኖረው፣ ከአሁናዊ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ስትራቴጂዎች ጋር አብረው የሚሄዱ ዓላማዎችን ለማስቀመጥ እና ማኅበረሰቡን ይበልጥ ለማገልገል ስትራቴጂክ ዕቆዱ መከለሱን ገልጸዋል። የተቋቋመው አማካሪ ቡድን ማእከሉ ዕቅዶቹን ከግብ በማድረስ በተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና መሪ የልኅቀት ማእከል ለመሆን ያስቀመጠውን ራእይ እንዲያሳካ ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።


አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት