ዩኒቨርሲቲው በ2016 ዓ/ም በመማር ማስተማር፣ ኅትመት፣ የትብብር ገንዘብ ድጋፍ በማምጣት እንዲሁም በአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ዘርፎች የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ግለሰቦች፣ የትምህርት ፕሮግራሞች፣ ትምህርት ክፍሎች፣ ኮሌጆችና የሥራ ክፍሎች ኅዳር 11/2017 ዓ/ም ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
በመማር ማስተማር ዘርፍ በ2016 የትምህርት ዘመን በመደበኛ እና ኢ-መደበኛ በመውጫ ፈተና (Exit Exam) መቶ በመቶ ያሳለፉ 25 የትምህርት ፕሮግራሞች፣ በኅትመት ዘርፍ እያንዳንዳቸው 22 እና 17 ኅትመቶች ያላቸው ሁለት የውጪ ሀገር መምህራን ዶ/ር ታሩን ኩማር (Dr Tarun Kumar) እና ዶ/ር ሙራሊታርን ጆዚማኒ (Dr. Muralitharn Jothimani) እንዲሁም 12 ኅትመቶች ያቀረቡት ዶ/ር ሳሙኤል ዳጋሎ፣ በትብብር ድጋፍ ፈንድ ዶ/ር ሳቡራ ሻራ በሦስት ፕሮጀክቶች ዋና እና በሁለት ፕሮጀክቶች ተባባሪ ተመራማሪ በመሆን ላስመዘገቡት የላቀ አፈጻጸም ዕውቅና አግኝተዋል፡፡
በመውጫ ፈተና መቶ በመቶ ላሳለፉ የትምህርት ፕሮግራሞች ለእያንዳንቸው አንድ እንዲሁም ለኮሌጆቹ ለእያንዳንዳቸው አንድ ላፕቶፕ ኮምፕዩተሮች ሽልማት የተበረከተ ሲሆን በኅትመት ዘርፍ ለተመረጡት ሁለቱ የውጭ ሀገራት ተሸላሚዎች ክሪስታል አዋርድና የምስክር ወረቀት እንዲሁም ለዶ/ር ሳሙኤል ዳጋሎ የታብሌት ሽልማት ተበርክቷል፡፡
በአስተዳደር ዘርፍ አቶ ሸዋንግዛው ታደሰ በተማሪዎች መመገቢያ አካባቢ በራሳቸው ተነሳሽነት ሌሎችን በማስተባበር ላከናወኑት አረንጓዴ ልማት ዕውቅና አግኝተው የስማርት ስልክ ሽልማት ሲበረከትላቸው በተመሳሳይም አቶ አባይነህ ከበደ በተመረጡበት ኮሚቴ በዋናው ግቢ ተማሪዎች መኝታ አካባቢ በማልማት የተለየ ገቢ ለዩኒቨርሲቲው በማስገኘታቸው ስማርት ስልክ ሽልማት እና አብረዋቸው ለተሳተፉ የኮሚቴ አባላት እንደተሳትፏቸው ተመርጠው የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ተጨማሪም የዩኒቨርሲቲው የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ምርምር ማዕከል የሥጋ ዶሮዎች፣ እንቁላልና ወተት የመሳሰሉትን ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በማቅረብ ባደረገው የላቀ አስተዋጽኦ በልዩነት ተመርጦ ዕውቅና የተሰጠው ሲሆን ሦስት ላፕቶፕ ኮምፕዩተሮች ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመርሃ ግብሩ ዕውቅና የሚያገኙ ግለሰቦችና የሥራ ክፍሎችን የመለየት ሂደት በቂ ጊዜ ተወስዶ በጥንቃቄ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም በኃላፊነትና በጥንቃቄ በመሥራት ለማኔጅመንቱ ላቀረቡ የኮሚቴ አባላት ፕሬዝደንቱ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ዕውቅናውን ላገኙት የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ዕውቅና መስጠቱ ተሸላሚዎችን የሚያበረታታና ለተሻለ ሥራ የሚያነሳሳ እንዲሁም ሌሎችንም ለላቀ አፈጻጸም የሚያተጋ መሆኑን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት