የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኤሌክትሪካልና ሜካኒካል ምኅንድስና ፋከልቲዎች ‹‹SNV-SEFFA›› ከተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ሙዝን አድርቆ ለምግብነት መጠቀም በሚያስችል በፀሐይ ኃይል የሚሠራ ቴክኖሎጂ ላይ ግንቦት 21/2016 ዓ/ም ዐውደ ጥናት አካሂደዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የኤሌክትሪካል ምኅንድስና ፋከልቲ መምህርና የጥናቱ አስተባባሪ ፍሥሃ ከድር እንደገለጹት ሙዝን አድርቆ በቂጣ፣ በኬክ፣ በገንፎ እና በተለያየ መልኩ ለምግብነት መጠቀም የሚቻል ሲሆን ዐውደ ጥናቱ ቴክኖሎጂውን ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውንና የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ እንዲችሉ ሃሳብ ለመለዋወጥ የተዘጋጀ ነው፡፡

የሜካኒካል ምኅንድስና ፋከልቲ መምህርት ቤተልሔም ዘመድኩን በበኩላቸው ሀገራችን ከምታመርተው የሙዝ ምርት 70 በመቶ የሚሸፈነው ከአርባ ምንጭና አካባቢዋ ቢሆንም ከምርቱ 40 በመቶ ያህሉ ለብክነት የሚዳረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሙዝ ማድረቂያ ማሽኑ የምርት ብክነትን በማስቀረት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያሻሽል ነውም ብለዋል፡፡

የ‹‹አንጆ ኑስ አግሮ ፕሮሰሲንግ›› አስተባባሪ አቶ ቻለው ገሲኖ ዩኒቨርሲቲው የአርሶ አደሩን የግብርና ሕይወት የሚያሻሽሉ ምርምሮችን ማካሄዱ ሊበረታታ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ገልጸው በቂ የገበያ ትስስር ለመፍጠር የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

በዐውደ ጥናቱ የሙዝ ማድረቂያ ማሽኑን ለአርሶ አደሩ በስፋት ማዳረስ፣ የገበያ ትስስር መፍጠር እንዲሁም አርሶ አደሩ የሙዝ ምርት አድርቆ ማቅረብ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን ‹‹SNV-SEFFA›› ግብረ ሠናይ ድርጅት ማድረቂያ ማሽኑን እንደሚያቀርብና ሌሎች ድጋፎችን እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት