አርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በቤልጂየሙ ‹‹Vliruos›› የገንዘብ ድጋፍ በሚተገበረው ‹‹AMU-VUB TEAM›› ፕሮጀክት ሥር የሚከናወኑ ሁለት የ3ኛ ዲግሪ ምርምር ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ መስከረም 12/2017 ዓ/ም የባለድርሻ አካላት ወርክሾፕ አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም የምርምር ፕሮጀክቶቹ ዓለም አቀፉን የዘላቂ ልማት ግብ ተከትለው የምግብ ዋስትና እና ንጹሕ የመጠጥ ውኃን አካተው መያዛቸው እንዲሁም በትብብር የሚሠሩ መሆኑ ወቅቱን የዋጁ እንዲሆኑና የዓለም አቀፍ ተቋማትን ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በዕውቀት ላይ የተመረኮዙ መፍትሔዎችን ይዞ ከመምጣቱ ባሻገር የአካባቢውን ማኅበረሰብ የሚያሳትፍና ሰፊ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል ነው ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ በአግባቡ እንዲተገበር እና በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ዓላማውን እንዲያሳካ ዩኒቨርሰቲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደርግ ገልጸዋል፡፡
የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ተሰሜ ፕሮጀክቱ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ከቤልጂም ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሚያስተሳስርና ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይም የኢንስቲትዩቱን መምህራንና ተመራማሪዎች አቅም በማሳደግ የተሻሉ ምርምሮችን ለማከናወን ብሎም ለተማሪዎቻችን በምርምር የዳበረ ተጨባጭ ዕውቀት ለማሸጋገር የሚረዳን ነው ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ትኩረት በመስጠት የንጹሕ መጠጥ ውኃ፣ ንጽሕናና የመስኖ ሥራን አጣምሮ የሚሠራ መሆኑ ወቅቱን የጠበቀና በተለይም የአካባውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ በመሆኑ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡
የAMU-VUB TEAM ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ዓለማየሁ ካሳዬ እንደገለጹት በአሁኑ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥ በተፈጥሮ ሀብቶቻችን በተለይም በውኃ እና ግብርናው መስክ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው፡፡ ችግሩ የምሁራንና ባለድርሻ አካላትን ጥምር ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ ፕሮጀክቱ ዓለም አቀፉን የዘላቂ ልማት ግብ መሠረት በማድረግ የአየር ንብረትን የሚቋቋም ‹‹WASH/Water, Adaptive Sanitation and Hygiene/ እና ግብርና ላይ ያተኮሩ በጋሞ ዞን ምዕራብ ዓባያ ወረዳ ዶሼ ቀበሌ የሚተገበሩ የ3ኛ ዲግሪ ምርምር ፕሮጀክቶችን ማስጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ባለድርሻ አካላትን በማገናኘት የፕሮጀክቱን ዓላማ ለማሳወቅ እና የጋራ ሥራዎች ላይ ለመመካከር ወርክሾፑ መዘጋጀቱን የገለጹት አስተባባሪው መሰል መድረኮች ፕሮጀክቱ እስከሚጠናቀቅ በየዓመቱ የሚኖሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በወርክሾፑ የ3ኛ ዲግሪ ምርምር ፕሮጀክቶቹ ፕሮፖዛል ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ከባለድርሻ አካላት አስተያየቶችና ቀጣይ የጋራ ሥራዎችን አስመልክቶ ሐሳቦች ተሰጥተዋል፡፡ በመርሐ ግብሩ ማጠናቀቂያም ፕሮጀክቶቹ በሚተገበሩበት አካባቢ በመገኘት ምልከታ ተካሂዷል፡፡
ፕሮጀክቱ ከቤልጂዬም መንግሥት በተገኘ በጀት የሚከናወን ሲሆን የአምስት ዓመት ቆይታ ያለው ነው፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት