አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጣሊያን ሮም በተካሄደው የዓለም የምግብ ቀን ሥነ-ሥርዓት ላይ የተባበሩት መንግሥታት የሥነ-ምግብና እርሻ ድርጅት የ2026 የላቀ ስኬት ሽልማት (FAO Achievement Award 2026) ለተቀበሉት ተመራማሪና ሳይንቲስት ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ በቱሪስት ሆቴል አርባ ምንጭ ደማቅ የምስጋናና የእውቅና ሥነ-ሥርዓት ጥቅምት 14/ 2019 ዓ/ም አካሂዷል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ከማል፣ የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ፣ የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ፕ/ር ጳውሎስ ታደሰ፣ ዳይሬክተሮች፣ የኮሌጅ ዲኖችና ተመራማሪዎች ተገኝተዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ከማል ባደረጉት ንግግር ይህ ዓለም አቀፍ ስኬት ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት እያካሄደ ላለው መዋቅራዊ ሽግግር ታላቅ አቅም እንደሚሆን አስረድተዋል። ሽልማቱ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ወደ «ምርምር ተኮርና ራስ-ገዝ (Research-led Autonomous University)» ተቋምነት የሚያደርገውን የሽግግር ጉዞ የሚያፋጥን፣ ትልቅ ትርጉምና ከፍተኛ ጥቅም ያለው አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል። ሽልማቱ የዩኒቨርሲቲውን ስምና ዝና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ማድረጉን ያመላከቱት ፕሬዝደንቱ፣ ይህም ተቋሙ ዓለም አቀፍ አጋሮችን፣ የገንዘብ ድጋፍ ሰጪዎችን (International Donors)፣ የምርምር ተቋማትና እውቅ ዩኒቨርሲቲዎችን በቀላሉ ስቦ አብሮ እንዲሰራ ትልቅ መንገድ የሚከፍት መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ታላቅ ሽልማት ሊገኝ የቻለው የዶ/ር አዲሱ የምርምርና የፈጠራ ሥራ በቀጥታ የማህበረሰቡንና የሀገርን መሠረታዊ ችግር የሚፈታ በመሆኑ እንደሆነ ያብራሩት ፕሬዝደንቱ፣ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም እንደ እንሰት ምርምር ሁሉ የማህበረሰቡን ችግር በተግባር የሚፈቱ፣ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ ያላቸውን ምርምሮች መስራቱን በሁሉም ዘርፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። በተጨማሪም ሽልማቱ የዩኒቨርሲቲውን በርካታ ተመራማሪዎች የሚያነቃቃና የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይም የተቋሙንና የሀገርን ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስጠሩ በርካታ «ዶ/ር አዲሱዎችን» በሌሎችም ዘርፎች ማፍራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል። በመጨረሻም ፕሬዝደንቱ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲንና ሀገርን የሚያኮራ ታላቅ ዓለም አቀፍ ስኬት በማስመዝገባቸው ልባዊ የእንኳን ደስ አለዎት እና የምስጋና መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዕለቱ ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ለሀገራችን ኢትዮጵያና ለመላዋ አፍሪካ ታላቅ የደስታና የኩራት ቀን መሆኑን ገልጸዋል። ዶ/ር አዲሱ ያገኙት ዓለም አቀፍ ሽልማት የዩኒቨርሲቲውን የምርምር ደረጃ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን በዓለም አቀፍ ደረጃ በጉልህ ያስተዋወቀ እና የሀገራችንን መልካም ስም በዓለም መድረክ ከፍ አድርጎ ያስነሳ ታላቅ እውቅና መሆኑንም አብራርተዋል።
ሽልማቱ በጣሊያን ሮም መበሰሩ ልዩ ያደርገዋል ያሉት ዶ/ር ተክሉ፣ «የአበበ ቢቂላ ታሪካዊ የኦሊምፒክ ድል በሮም ምድር ከተመዘገበ ከብዙ ዓመታት በኋላ፣ በዚያው በሮም ከተማ በሳይንሱ ሜዳ ድላችንን መድገም ችለናል» ሲሉ ገልጸዋል። አክለውም ዩኒቨርሲቲው በዶ/ር አዲሱ የተጀመሩ የቴክኖሎጂና የምርምር ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ፣ በተለይም እነዚህን የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ተዳራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የመድረኩ ዋና ባለቤትና የተሸላሚው ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ ባደረጉት የምስጋና ንግግር፣ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና አመራሮች ላደረጉላቸው ሞቅ ያለ አቀባበልና የእውቅና ፕሮግራም የከበረ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ያገኙት ዓለም አቀፍ ሽልማት የግል ብቻ ሳይሆን የዩኒቨርሲቲውና የሀገር ኩራት መሆኑን ያመላከቱት ዶ/ር አዲሱ፣ ለዚህ ስኬት መብቃት አብረዋቸው ለዓመታት ለደከሙት የምርምር ቡድናቸው፣ አጋሮች ድጋፍ ላደረጉላቸው ተቋማት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አክለውም ይህ ሽልማት ለወደፊቱ ትልቅ ትርጉም ያለውና ለቀጣይ ሥራዎች ትልቅ በር የሚከፍት መሆኑን ገልጸው፣ እንሰት ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ያለው ታላቅ ሚና አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት ማግኘቱንና እውቅና መሰጠቱን ገልጸዋል። ይህ ሽልማት የረጅም ጊዜ የትጋትና የጥረት፣ ተስፋ ያለመቁረጥ እንዲሁም የገጠሟቸውን ፈታኝ እንቅፋቶችና ችግሮች በፅናት የማለፍ ውጤት መሆኑን የተናገሩት ተመራማሪው፣ በቀጣይም በእንሰት ዘርፍ በርካታ ውጤታማና የላቁ ሥራዎችን ለመስራት ትልቅ መነቃቃትና መነሻ እንደሚሆናቸው አስረድተዋል።
በምስጋናና የእውቅና መድረክ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ ተመራማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዦች ስለ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ ስብዕናና የምርምር ጉዞ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ተሳታፊዎቹ በሰጡት አስተያየት ዶ/ር አዲሱ ለአመታት ላሳዩት የላቀ የሙያ ቁርጠኝነት (Commitment)፣ ላንፀባረቁት ያልተደናቀፈ ትዕግስት (Patience) እና ላሳዩት የማይወለወል ፅናትና እረፍት የለሽ ጥረት (Consistency & Resilience) ከፍተኛ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም የሳይንስና የምርምር ውጤቶችን ለአለም አቀፍ ተቋማት፣ ለለጋሾችና ከአርሶ አደሩ ጋር በቀላሉ ማገናኘት ያስቻላቸው የላቀ የመግባባትና የማስረዳት ክህሎታቸው (High Communication Skill) ለዚህ ታላቅ የአለም አቀፍ ሽልማትና ለሎችም ድልና ስኬቶች ያበቃቸው ዋና ምክንያት መሆኑን በአፅንኦት መስክረዋል።
በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ከማል ለዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ ለዩኒቨርሲቲውና ለሀገር ላስገኙት ታላቅ የዓለም አቀፍ ሳይንስ እውቅና የዩኒቨርሲቲውን ልዩ የክርስታል የክብር ሽልማት (Crystal Award) አበርክተውላቸዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የጥበብ ምንጭ /Spring of Wisdom
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

