አርባ ምንጭ፤ ጥቅምት 28 ቀን 2019 ዓ.ም (AMU)— በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ሲካሄድ በቆየው 3ኛው ዓለም አቀፍ የእንሰት ምርምር ሲምፖዚየም ማጠቃለያ ላይ በእንሰት ሰብል የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ በቅንጅት ለመስራት እና ሲምፖዚየሙን በየዓመቱ በፈረቃ ለማስተናገድ የሚያስችል የእንሰት ኮንሶርቲየም (National Enset Consortium) በትናንትናው ዕለት ተመስርቷል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
ይህ ታሪካዊ የመግባቢያ ሰነድ (MoU) በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ፣ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ፣ በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ እና በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መካከል የተፈረመ ሲሆን፤ በቀጣይም ሌሎች የእንሰት አምራች አካባቢዎች የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የምርምር ማዕከላት እና አጋር ድርጅቶች ኮንሶርቲየሙን እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል።
የስምምነቱ ዋና ዓላማ በእንሰት ሰብል ላይ የሚደረጉ የምርምር እና የቴክኖሎጂ ግኝቶችን በተበታተነ መልኩ ከመስራት ይልቅ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በጋራ በመቀናጀት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ በእንሰት ባክቴሪያል ዊልት (Bacterial Wilt) አጠውልግ በሽታ ወዘተ ላይ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት እና የእንሰት ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎችን (Commercialization) ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ነው። በተጨማሪም ኮንሶርቲየሙ ዓለም አቀፍ የእንሰት ምርምር ሲምፖዚየምን በየዓመቱ በአባል ዩኒቨርሲቲዎች አስተናጋጅነት በፈረቃ የማዘጋጀት ኃላፊነት ይወስዳል።
በዚሁ መሠረት፣ የሚቀጥለውን 4ኛውን ዓለም አቀፍ የእንሰት ምርምር ሲምፖዚየም (4th International Enset Symposium) በ2027 ዓ.ም በዋና አስተናጋጅነት ለመምራት እና ለማዘጋጀት ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊነቱን ተረክቧል።
በስምምነቱ ወቅት እንደተገለጸው፤ ይህ የጋራ ትብብር ዩኒቨርሲቲዎቹ ያላቸውን የሰው ኃይል፣ የቤተ-ሙከራ አቅም እና የምርምር ውጤቶች በጋራ በመጠቀም የእንሰት ሰብልን የምግብ ዋስትና ስትራቴጂካዊ መፍትሔ ለማድረግ የሚያስችላቸውን አቅም እንደሚፈጥርላቸው እና ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የምርምር ፕሮጀክቶችን በጋራ ለመስራት ትልቅ ምዕራፍ እንደሚከፍት ተጠቁሟል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

