በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹RUNRES›› ፕሮጀክት በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተፕራይዝ ደረጃ ተደራጅተው በመጀመሪያ ዙር የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩት ‹‹አንጆ ኑስ የሙዝ ማቀነባበሪያ›› እና ‹‹እኛን ነው ማየት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማቀነባበሪያ›› ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሚያስችሉ የቢዝነስ ሃሳቦች ዙሪያ በጋሞ ዞን ከሚገኙ ኢንቬስተሮች ጋር ሐምሌ 10/2016 ዓ/ም ወርክሾፕ ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
ራእያችንን የሚጋሩና አዎንታዊ ተጽዕኖ ለመፍጠር ቁርጠኛ የሆኑ ባለሀብቶችን እንፈልጋለን ያሉት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ተባባሪ ፕ/ር በኃይሉ መርደኪዮስ በመድረኩ የተገኙ ኢንቬስተሮች ኢንተርፕራይዞቹን በመደገፍና ተግዳሮቶቻቸውን በመፍታት የትብብር አቅምን እንዲፈጥሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ኒቨርሲቲ ‹‹RUNRES›› ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አባይነህ ፈይሶ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ላለፉት አራት ዓመታት በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ደረጃ ተደራጅተው የሚሠሩ ማኅበራትን በቢዝነስ ሃሳብ፣ በቴክኖሎጂና ቴክኒካዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ‹‹አንጆ ኑስ የሙዝ ማቀነባበሪያ›› እና ‹‹እኛን ነው ማየት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማቀነባበሪያ›› ኢንተርፕራይዞች የተሻለ የመጀመሪያ ዙር አፈጻጸም ስላስመዘገቡ እነሱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ታልሞ ወርክሾፑ መዘጋጀቱን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የ‹‹RUNRES›› ፕሮጀክት የቢዝነስ ሃሳብ ባለሙያ ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ ‹‹Co-Investment and Business Financing Model›› በሚል ርእስ የውይይት መነሻ ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን መድረኩ በጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች የበለጠ እንዲያድጉና ራሳቸውን እንዲችሉ ከሌሎች ኢንቬስተሮች ጋር በማገናኘት ተደጋግፈው እንዲቀጥሉ ዕድሉን የሚያመቻች ነው ብለዋል፡፡
የአንጆ ኑስ የሙዝ ማቀነባበሪያ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ጆን ከድር ኢንተርፕራይዙ ሙዝና ሌሎች የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር ለገበያ የሚያቀርብ መሆኑን ጠቁመው አሁን ላይ የሙዝ ምርትና ሞሪንጋ/ሀለኮ/ በተለያየ መጠን በዱቄት መልክ በማቀነባበር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ኢንተርፕራይዙን ሀገራዊና ሕዝባዊ ለማድረግ ስለሚታሰብ በዘርፉ አብሮ ለመሥራት የሚፈልጉ የሀገር ውስና የውጭ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ ሥራ አስኪያጁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የእኛን ነው ማየት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማቀነባበሪያ ኢንተርፕራይዝ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቦጋለ ቢታኔ ማኅበራቸው በ1998 ዓ/ም የተመሠረተ መሆኑንና ላለፉት 17 ዓመታት የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማቀነባበር ለተጠቃሚው ማኅበረሰብ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ በ2016 ዓ/ም ከ18 ሺህ ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማቀነባበር ለተጠቃሚው ማዳረሳቸውን የተናገሩት አቶ ቦጋለ ማኅበሩ በአርባ ምንጭ ከተማ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር በዘርፉ መሳተፍ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጋሞ ልማት ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳሙኤል ግርማ ልማት ማኅበሩ በማኅበራዊ ኢንተርፕራይዝ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ተናግረው ማኅበሩ በአርባ ምንጭ ከተማ ባለው 705 ሄክታር መሬት የተለያዩ የፍራፍሬና የአትክልት ምርቶችን ስለሚያመርት የሙዝ ምርትን በማቅረብና የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም ከሁለቱ ኢንተርፕራይዞች ጋር በጋራ ለመሥራት ዕቅድ የሚያወጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት