የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ለ2016 ዓ/ም ተመራቂ ተማሪዎች በሥራ ሥነ ምግባር መርሆዎች እና በሙስና ወንጀል ሕጎች ዙሪያ ከሰኔ 21-24/2016 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የዳይሬክቶሬቱ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ እታፈራሁ መኮንን የመልካም ሥነ ምግባርና የሞራል ዕሴት ሥልጠና ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ በተማሪነት ዘመን ያገኙትን ሳይንሳዊ ዕውቀት ሲተገብሩ በሕዝብ አገልጋይነት ስሜት እና መልካም ሥነ ምግባርን በተከተለ መልኩ እንዲሆን ለማስገንዘብ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተመራቂዎች ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ ማኅበራዊ ዕሴቶችን እንዲሁም በመንግሥት መመሪያ፣ አዋጅና ደንቦች የተቀመጡ ድንጋጌዎችን በማክበር በታማኝነት እንዲያገለግሉና የሙስና ወንጀል ሕጎችን በመገንዘብ ሙስና ከሚያደርሰው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳቶች ራሳቸውንና ሌሎችን ለመከላከል ተመራቂ ተማሪዎች ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ት/ክፍል መምህር ዶ/ር ያሲን ሁሴን ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ ሐቀኝነት፣ አለማዳላት፣ ግልጸኝነትና የማኅበረሰብን ጥቅም ማስቀደምን ጨምሮ 12ቱን የሥነ ምግባር መርሆዎች እና መሠረታዊ የሥራና ሙያዊ ሥነ ምግባር መርሆዎችን አውቀው ራሳቸውን ለሙስናና ለብልሹ አሠራር ከሚያጋልጡ ነገሮች እንዲጠብቁ ለማስቻል በማለም ሥልጠናው መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የአግሮ ኢኮኖሚክስ ተመራቂ ተማሪ ዓለሙ ካሣሁን ለማኅበረሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት፣ ሀብትን በአግባቡ መጠቀም፣ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎችን ማሳደግ እና ራስን በማስተማር አቅምን ማሳደግ የመሳሰሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ከሥልጠናው ጠቃሚ ሐሳቦችን ማግኘቱን አስተያየት ሰጥቷል፡፡
ሌላኛዋ የሥልጠናው ተሳታፊ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የስፖርት ሳይንስ ተመራቂ ተማሪ ብርሃን ደጀኔ በበኩሏ ሥልጠናው ለተመራቂ ተማሪዎች ወሳኝ መልእክት ያለው በመሆኑ የምረቃ ወቅት ሳይደርስ ቀደም ብሎ ቢሰጥና ሁሉም ተመራቂ ተማሪ የሚገኝበት ቢሆን መልካም ነው ብላለች፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት