ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች በቅድመ እና ድኅረ ምረቃ የትምህርት መርሐግብሮች ያሠለጠናቸውን 1263 የቅድመ እና 199 የድኅረ ምረቃ በአጠቃላይ 1462 ተማሪዎችን ዛሬ ሰኔ 20/2018 / አስመርቋል፡፡ የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዴሪ የማዕድን ሚንስትር እና የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢ / ሀብታሙ ተገኝ በቁልፍ መልእክታቸው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ ካሉ ግንባር ቀደም ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ መሆኑንና በአሁኑ ጊዜም በተለያዩ የምርምር፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት እና ራስን በራስ የማስተዳደር (Self-Autonomous) መዋቅራዊ ሥራዎች ላይ ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በዚህ አንጋፋ ዩኒቨርሲቲ በዕውቀትና በሥነ ምግባር ታንፀው ለስኬት ቀናቸው በመድረሳቸው ምሩቃንን እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት ሚንስትሩ በሄዳችሁበት ቦታ ሁሉ የዩኒቨርሲቲያችሁን መልካም ስም የምታስጠሩ፣ የሥራ ፈጣሪነትና የቅንነት ተምሳሌት ሆናችሁ እንደምታገለግሉ ሙሉ እምነት አለኝ ብለዋል። ብሩህና ስኬታማ የሥራ ዘመንንም ተመኝተዋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት / / አብደላ ከማል አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋና ዋና የምርምር የትኩረት አቅጣጫዎችን በመለየት እየሠራ መሆኑን ገልጸው በኢትዮጰያ ቀዳሚ ራስ ገዝ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆንም በትጋት እየሰራ ነው ብለዋል። 

ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በዓለም አቀፍ የሜትሮሎጂ ድርጅት የምሥራቅ አፍሪካ የሜትሮሎጂ እና የአየር ንብረት ሥልጠና ማዕከል ሆኖ መመረጡ ጉልህ ስኬት መሆኑን ያወሱት ፕሬዝደንቱ የለውጥ ጉዞው ተቋሙ ተማሪዎችን በምርምር፣ በፈጠራ እና በአመራር ላይ የበለጠ ዕድሎችን እንዲያገኙ የሚያስችል ብሎም የሳይንስ እና የምርምር የልኅቀት ማዕከልነቱን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲተው በሕክምና፣ በጤና፣ በሳይንስ፣ በውኃ፣ በአካባቢ ጥናት፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ እና በቱሪዝም ዘርፎች ያለውን የምርሞር አቅም በማሳደግ ለሀገራችን የልማት ፍላጎቶች ምላሽ የሚሰጡ ውጤታማ መፍትሔዎችን ለማቅረብ እየሠራ ነው። ለዚህም ዩኒቨርሲቲው 700 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ቤተ ሙከራዎችን ማዘመኑንና ማደራጃቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ተመራቂዎች ከዚህ ተፅዕኖ ፈጣሪ ዩኒቨርሲቲ መመረቃቸው በየትኛውም የሥራ መስክ ተጨማሪ ክብር፣ ተቀባይነትና ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል። በመሆኑም በቆይታቸው የቀሰመትን ዕውቀት፣ ልምድ እና የሕይወት ትምህርት በመልካም ምግባርና በኃላፊነት ተግባር ላይ በማዋል የዩኒቨርሲቲያቸውን ስም ይበልጥ ከፍ እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል። የሚኖሩበትን ማኅበረሰብ በብቃትና በትጋት ለማገልገል እና ለሀገራቸው እድገት የበኩላቸውን ለማበርከት ሁሌም ዝግጁ እንዲሆኑም አሳስበዋል።

የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን (አሉምናይ) ማኅበር ፕሬዝደንት አቶ ኤርምያስ ዓለሙ ምሩቃን በብርቱ ትግልና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች አልፈው የአዲስ ምዕራፍ ጅማሬ ለሆነው ለዚህ የስኬት ቀናቸው በመድረሳቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። ከዚህ ዕለት ጀምሮ የዩኒቨርሲቲው አሉምናይ እንደመሆናቸው የቀድሞ ምሩቃን ኅብረቱን ተቀላቅለው በትምህርት፣ በምርምርና በልዩ ልዩ የሥራ መስኮች ያሉ ዕድሎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙም ጥሪ አቅርበዋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ከየኮሌጆቹና ትምህርት ቤቶች የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የወርቅ ሜዳሊያ የተበረከተ ሲሆን ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ሴት ምሩቃንም ልዩ ሽልማት ተበርክቷል።

ዩኒቨርሲቲው 39 ዓመታት ጉዞው የዛሬዎቹን ጨምሮ 89 ሺህ 276 ምሩቃንን ለሀገር አበርክቷል።

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የጥበብ ምንጭ!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

 

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት