አቶ አሰፋ ጨጉልኤ ከአባታቸው ከአቶ ጨጉልኤ ቂዳ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ሳባሬ ሳቂሞ በቀድሞ ጋሞ ጎፋ ክፍለ ሀገር በቦንኬ ወረዳ በገረሴ ከተማ በ1966 ዓ/ም ተወለዱ፡፡

አቶ አሰፋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በገረሴ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በአርባ ምንጭ ከተማ ኩልፎ መለስተኛ 2 ደረጃ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን የ2 ደረጃ ትምህርታቸውን በአርባ ምንጭ አጠቃላይ 2 ደረጃ ት/ቤት ተከታትለዋል፡፡

አቶ አሰፋ ከአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሳፖርት በደረጃ II መስከረም 2008 ዓ/ም፣ ከሳታ ቴከኖሎጂና ቢዝነስ ኮሌጅ በሀርድዌርና ኔትዎርክ ሰርቪስ በደረጃ III ነሐሴ 2008 እንዲሁም ከአርባ ምንጭ መካነ ኢየሱስ ቴከኖሎጂና ቢዝነስ ኮሌጅ በአካውንቲንግና በጀት ሰርቪስ በደረጃ IV ጥቅምት 2014 ዓ/ም  ተመርቀዋል፡፡

አቶ አሰፋ ከመስከረም 1/1999 ዓ/ም - ታኅሳስ 24/2000 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ከተማ ዋና ማዘጋጃ ቤት በመዝገብ ቤት ሠራተኛነት፣ ከታኅሳስ 25/2000 ዓ/ም - የካቲት 3/2002 ዓ/ም በአርባ ምንጭ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በፔርሶኔል ሠራተኛነት፣ ከየካቲት 4/2003 ዓ/ም - ታኅሳስ 23/2004 ዓ/ም በአርበ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት በመዝገብ ቤት ሠራተኛነት፣ ከታኅሳስ 24/2004 ዓ/ም - ጥር 30/2006 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት በሪከርድና ምዝገባ አደራጅነት እንዲሁም ከየካቲት 1/2006 ዓ/ም ጀምሮ ሕይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሬጂስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት በሪከርድና ዶክመንቴሽን ሠራተኛነት አገልግለዋል፡፡

አቶ አሰፋ ባለትዳርና የአምስት ሴት ልጆችና የሁለት ወንድ ልጆች አባት የነበሩ ሲሆን ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ50 ዓመታቸው ሰኔ 20/2016 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአቶ አሰፋ ጨጉልኤ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ ለሟች ቤተሰቦች፣ ለወዳጅ ዘመዶችና ለሥራ ባልደረቦች እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ መጽናናትን ይመኛል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት