የደቡብ ኢትዮጵያ ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ባዘጋጀው የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ላይ የተወዳደሩት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ብዝኀ ሕይወት ምርምርና ጥበቃ ማእከል ተመራማሪ አታላይ አዘነ ውድድሩን በሦስተኛነት በማጠናቀቅ የሰርተፊኬትና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የውድድሩ ዓላማ የሥራ ፈጠራ ሃሳቦችን አወዳድሮ በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ውድድር ክልሉን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎችን መለየት ሲሆን በዚህም መሠረት መ/ር አታላይ ክልሉን ወክለው ከሚወዳሩት አንዱ ሆነዋል፡፡
ተመራማሪ አታላይ እንደለጹት በዩኒቨርሲቲው ብዝኀ ሕይወት ምርምርና ጥበቃ ማእከል ከሚያከናውኗው ምርምሮች አንዱ ፓርቲኒዬምና እንቦጭ መጤ አረሞችን በመጠቀም የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት ነው፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያው በበቆሎና ሌሎች ሰብሎች ላይ ተሞክሮ ውጤት ማስገኘቱን የጠቀሱት ተመራማሪው በዚህም መነሻነት የተለያዩ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ሽልማቶችን ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
ፓርቲኒዬምና እንቦጭ አረሞች የአካባቢ ብክለትን በማስከተል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳትን እያስከተሉ ነው ያሉት ተመራማሪው አረሞቹን ተጠቅሞ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማምረት አካባቢን ከብክለት ለማዳን፣ የማሕበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ ብሎም ከሀገር ውጭ በከፍተኛ ወጪ የሚገቡ ማዳበሪያዎችን በማስቀረት ምርታማ ለመሆን በእጅጉ ይረዳል ብለዋል፡፡
እንደ ተመራማሪው የደቡብ ኢትዮጵያ ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ያዘጋጀው ውድድር ላይ የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ተወዳዳሪዎች ከየዞኑ ተመርጠው የተሳተፉ ሲሆን በመድረኩ በአጠቃላይ ከቀረቡ 30 የሥራ ፈጠራ ሃሳቦች መካከል ምርምራቸው በሦስተኛነት ማሸነፍ ችሏል፡፡
‹‹ሃሳብ ጉልበት እና ገንዘብ መሆኑን ያየሁበት ውድድር ነው›› ያሉት ተመራማሪው በቂ ድጋፍ አግኝተው ወደ ተግባር ቢለወጡ የማኅበረሰቡን ችግር በተጨባጭ የሚፈቱ በርካታ የሥራ ፈጠራ ሃሳቦች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ ምርምራቸውን ወደ መሬት በማውረድ አካባቢን ከብክለት ለመጠበቅና ጤናማ ትውልድን ለመፍጠር የበኩላቸውን መወጣት እንዲሁም በሒደቱ ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድልን መፍጠር ቀጣይ ዕቅዳቸው መሆኑን ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡ በሥራቸው ከጎናቸው ለነበሩ ሁሉም ምስጋቸውንም አቅርበዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት