የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአዲስ አበባና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ለሚገኙ ትምህርት ፈላጊዎች በገጽ ለገጽ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የ2ኛና የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ለማስጀመር የሚያስችል የውስጥ ግምገማ ዐውደ ጥናት ታኅሣሥ 30/2017 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ተ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢንጂነር ቦጋለ ገ/ማርያም እንደገለጹት ዐውደ ጥናቱ በውኃና ቴክኖሎጂው ዘርፍ መማር ለሚፈልጉ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል እና በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ለሚገኙ ትምህርት ፈላጊዎች ልማዳዊ ከሆነው የትምህርት አሰጣጥ በመውጣት ጥራቱን የጠበቀና የሀገሪቱን የትምህርት ፖሊሲ የተከተለ ትምህርትና ሥልጠና ለመስጠት ሙያዊ የሃሳብ ልውውጥ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡ የትምህርት ፕሮግራሞቹን ተደራሽ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቶች እየተካሄዱ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ አውስተዋል፡፡
የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተወካይ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ተሰሜ በበኩላቸው የፕሮግራሞቹ መጀመር በአዲስ አበባና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ በዘርፉ መማር ፈለግው ዕድሉን ላላገኙ ሰዎች መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቁመዋል:: የሚጀመረውን የመማር ማስተማር ሥራ በምርምርና በቤተ ሙከራ የተደገፈ ለማድረግ ግብአት የማሟላት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የውኃ አቅርቦትና አካባቢ ምኅንድስና ፋከልቲ ዲን መ/ር ዘላለም አበራ በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት፣ በመስኖና ግድብ ፕሮጀክቶች፣ በስኳርና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማትና በሌሎች መ/ቤቶች የተሰማሩ ባለሙያዎች እንዲሁም ፕሮግራሞቹን ለመከታተል ጥያቄ ያቀረቡና ፍላጎታቸውን ያሳዩ በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ ዜጎች የፕሮግራሙ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ አመላክተዋል፡፡
በውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክተር ሱፊያን አብዱልመናን በውኃው ዘርፍ እንደ ሀገር በርካታ ባለሙያዎች የሚያስፈልጉ በመሆኑና የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በዘርፉ ቀዳሚ እንደመሆኑ የትምህርት ፕሮግራሞችን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተደራሽ ማድረግ ጠቀሜታው የላቀ ነው ብለዋል፡፡
የትምህርት ፕሮግራሞቹ ከ30 እስከ 40 በመቶ በገጽ ለገጽ እንዲሁም ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን በሳምንት መጨረሻና በበዓላት ወቅት በዲጂታል ቴክኖሎጂ አጋዥነት ለመስጠት መታቀዱ በዕለቱ ተጠቁሟል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት