በሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) ድጋፍ የበለጸገውን የወባ በሽታ ስርጭት መተንበያ ስርዓት ለማበጀት "AI-based Malaria Incidence Prediction Under Current And Future Climate In Southern Ethiopia" በሚል ርዕስ ሲሰራ የቆየው የትብብር ፕሮጀክት ማጠቃለያ ወርክሾፕ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ መስከረም 08 ቀን 2019 ዓ.ም ተካሂዷል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
በዕለቱም የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ የምርምር ባለሙያዎችና የሶፍትዌር አልሚዎች ተገኝተዋል። በተጨማሪም ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የ12 ዞኖችና የ3 ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ አካላት፣ የፌደራል ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አመራሮችና ተመራማሪዎች በስነ-ስርዓቱ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።
የፕሮጀክቱ ዋና መሪና የዩኒቨርሲቲው የኤሌክትሮኒክስ ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ አበበ፣ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ጉዞ፣ አሁናዊ ሁኔታና የስራ ሂደት ለታዳሚው በዝርዝር አብራርተዋል።
በዕለቱ በተካሄደው የስርዓት ፕላትፎርም ማሳያ (Demonstration) ላይ የፕሮጀክቱ አባል የሆነው የ5ኛ ዓመት የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ተማሪ ጴጥሮስ መሳይ የተገነባውን ስርዓት ተግባራዊ እንቅስቃሴ በግልጽ ያሳየ ሲሆን፣ በሌላኛው የፕሮጀክት አባል በዶክተር በፍቃዱ ማሴቦ አቅራቢነት "የAIM-CLIM ምርምር ውጤትን ወደ ሕብረተሰብ ጤና አተገባበር መተርጎም" በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቧል። በተጨማሪም በምርምር ፕሮጀክቱ ረዳት ተመራማሪ በዶክተር በሀይሉ መርደኪዮስ መሪነት የሙከራ ሥራው ቀጣይነትና በስርዓቱ ማስፋፊያ (Scale-up) ዕቅድ ላይ ያተኮረ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።
የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ኢ/ር አብደላ ከማል በመክፈቻ ንግግራቸው፤ መንግስት ለልማት ዕቅዱ ያስቀመጣቸውን ዋና ዋና ምሰሶዎች ማለትም ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና አይሲቲን (ICT) አጉልተው አንስተዋል። አክለውም ይህ ፕሮጀክት ሀገሪቱ ያቀደችውን የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ኢንሼቲቭ ከግብ ለማድረስ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፣ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ዘርፍ በትኩረት እንዲሰሩ ከተለዩት ተቋማት አንዱ በመሆኑ መሰል ስራዎች ሀገራዊ እና ማህበረሰባዊ ችግሮችን በመፍታት ረገድ የጎላ ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል።
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶክተር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ ላለፉት ሁለት ዓመታት በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎትና በወባ በሽታ መከላከል ላይ አተኩሮ ሲሰራ መቆየቱን አብራርተዋል። የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው የዝናብና ድርቅ መዛባት የተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመቆጣጠር ፈተና መሆኑን ጠቁመው፤ የጤና፣ የአካባቢና የታካሚ መረጃዎችን በማሽን መማሪያ (Machine Learning) እና ጥልቅ መማሪያ (Deep Learning) አልጎሪዝሞች በመተንተን በሽታዎችን አስቀድሞ ለመተንበይ AI ዘመኑ የሚጠይቀው አስተማማኝ መፍትሔ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ፕሮጀክቱ ከተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች (SDGs) — በተለይም ከግብ 3፣ ግብ 5 እና ግብ 13 — እንዲሁም ከሀገሪቱ ወባን የማስወገድ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ ጋር በቀጥታ የተሰናሰለ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዶክተር መሐመድ አበበ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ ከአርማወር ሀንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት (AHRI) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተከናወነ ሲሆን፣ በሂደቱም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI)፣ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት እና የፌደራል ጤና ሚኒስቴር አስፈላጊ መረጃዎችን በማቅረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
በስነ-ስርዓቱ ማጠቃለያ ላይ ለፕሮጀክቱ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች፣ የስርዓት አልሚዎችና ደጋፊ ተቋማት የእውቅናና የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የጥበብ ምንጭ!
መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

