በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹BioRES›› ፕሮጀክትና በሊድስ(LEEDS) ዩኒቨርሲቲ ትብብር የብዝኀ ሕይወት ቁጥጥርና ማኅበረሰብ አቀፍ ጥበቃ ማከናወን በሚያስችሉ የካሜራ አጠቃቀም ዘዴዎች ዙሪያ የዘርፉ ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ጥቅምት 16/2018 ዓ/ም ወርክሾፕ ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የፕሮጀክቱ አፈጻጸምና የተገኙ ውጤቶች፣ የሥነ ምግባር አተገባበር፣ የካሜራዎች አጠቃቀም፣ ካሜራዎች በያዟቸው መረጃዎች መሠረት ትንተና ማድረግ እና ጂአይ ኤስ(GIS)ና የመረጃ አሰባሰብ በወርክሾፑ ከተዳሰሱ ነጥቦች መካከል ናቸው፡፡ ከሊድስ ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር አላስተር ዋርድ(Alastair Ward) የካሜራ አቀራረጽ ታሪክ፣ መርህና አጠቃቀማቸው፣ አተካከልና አቀማመጥ እንዲሁም ትንተናዎችና አተረጓጎም ምን እንደሚመስል ከሊድስ ዩኒቨርሲቲ በቪዲዮ ምልከታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ በተያያዘም ዶ/ር ታደሰ ወልዴ ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ፕሮፖዛል በሚዘጋጅበት ወቅት ልንከተል የሚገባን የሥነ ምግባር ሥርዓቶች፣ መተግበሪያና እይታዎች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም እንደገለጹት ወርክሾፑ ማኅበረሰቡ ካሜራን በመጠቀም የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ የሚያስችለውን ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ሲሆን ለዚህም ሥራ የሚያገለግሉ ካሜራዎች በፕሮጀክቱ አማካኝነት በድጋፍ ተገኝተዋል፡፡ መሰል ፕሮጀክቶች ዩኒቨርሲቲውን አንድ እርምጃ ማራመድ የሚያስችሉ በመሆኑ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ዶ/ር ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሶሻል አንትሮፖሎጂ ት/ክፍል መምህርና የ«Biodiversity Potential for Resilient Livelihoods in the Lower Omo» (BioRES AMU) ፕሮጀክት አስተባባሪ እሸቱ እውነቱ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ለብዝኀ ሕይወት ቁጥጥር የሚያገለግሉ 53 ካሜራዎች መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ወርክሾፑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ አስተዳደር፣ የእንስሳት ሳይንስና የብዝኀ ሕይወት ጥበቃን ጨምሮ የተለያዩ የትምህርት ክፍሎችን በማሳተፍ የተገኙትን ካሜራዎች ማሳወቅና መገልገል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ እንደሚያስጨብጥ ተናግረዋል፡፡ የካሜራዎቹ አጠቃቀም፣ እስከ አሁን የሰጡት አገልግሎት እና በቀጣይ የሚከናወኑ ሥራዎች ላይ የጋራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑንም መ/ር እሸቱ ገልጸዋል፡፡

እንደ ተመራማሪው በደቡብ ኦሞ ዞን ሙርሲ፣ ቦዲና ባጫን በመሳሰሉ አካባቢዎች የሚገኘው በተለምዶ «የታማ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ» ተብሎ የሚጠራው ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ጥብቅ የማኅበረሰብ ስፍራዎች መካከል 2ኛው ሲሆን በፕሮጀክቱ በጥብቅ ስፍራው የሚገኙ ቀጭኔ፣ ዝሆን፣ ቆርኬና የተለያዩ እንስሳትን በካሜራ አንሥቶ መያዝ ተችሏል፡፡ ካሜራዎቹ በአካባቢው ተተክለው በቀንና በማታ ሲቀርጹ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በወርክሾፑ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችን ጨምሮ ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ አስተዳደር፣ ከእንስሳት ሳይንስ፣ ከብዝኀ ሕይወትና ከሶሻል አንትሮፖሎጂ የት/ክፍሎች እንዲሁም ከሊድስና ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ተመራማሪዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ታድመዋል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት