የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በሥሩ ከሚገኙ የሥራ ክፍሎች ጋር ሐምሌ 9/2017 ዓ/ም በ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና በ2018 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ ባለፈው በጀት ዓመት በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡ መሆናቸውንና ስኬቶቹም በውስን በጀት፣ በተጣበበ ጊዜና ሌሎች ጫናዎችን በማለፍ የተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል። የኮሌጁ የቀድሞ አመራር አካላት እና ሁሉም ት/ክፍሎች ለስኬቶቹ መመዝገብ ላበረከቱት አስተዋጽዖ ምስጋና በማቅረብ በቀጣይ ዕውቅና የመስጠት መርሐ ግብር መታቀዱን አክለዋል። የተሻለ ዕውቀትና የሥራ ፈጠራ ክሂሎት ያላቸው ተማሪዎችን ማፍራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መስራት በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ዲኑ ተናግረዋል።
እንደ ዶ/ር ወንድወሰን ገለጻ በሀገርና ዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ፣ ተመራጭና ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን የምርምርና የኅትመት ውጤቶችን ማሻሻል፣ የማኅበረሰቡን ችግር መፍታት፣ ገቢን ማሳድግ፣ የመ/ራንንና የተማሪዎችን አቅም ማዳበር እንዲሁም ከዓለም አቅፍ ተቋማት ጋር ጠንካራ ትብብር የመፍጠር ጉዳይ የ2018 በጀት ዓመት የትኩረት ነጥቦች ናቸው::
የኮሌጁ ም/ዲን አቶ ፈንቴ ሚደቅሳ ባለፈው በጀት ዓመት የተከናወኑ አበረታች ተግባራት እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በትክክል ለመለየትና በቀጣይ ስኬታማ ተግባር ማከናወን በሚቻልበት ሁናቴ ላይ የጋር ግንዛቤ መፍጠር የውይይቱ ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል። አያይዘውም በ2018 በጀት ዓመት በኮሌጅ ደረጃ የተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና እንዲያገኙ መሥራት፣ በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ማኔጅመንት የ2ኛ ዲግሪ ኢ-መደበኛ ትምህርት ፕሮግራም ማስጀመር፣ የገቢ ማመንጫ ዘርፎችን መለየትና ወደ ሥራ ማስገባት፣ የኮሌጁን ልኅቀት የሚያሻሽሉ የኢንተርፕርነርሺፕና የሙያ ማበልጸጊያ ማዕካላትን ማሳደግ በዕቅድ ከተያዙ ተግባራት መካከል መሆናቸውን አስረድተዋል።
የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ማኅበረሰብ ጉድኝትና ኢንደስትሪ ትስስር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ መ/ርት አስቴር ሰይፉ በበኩላቸው ጽ/ቤቱ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን፣ የማማከር አገልግሎት እንዲሁም ጥናትና ምርምር ውጤቶችን መነሻ ያደረጉ እና በ2016 በጀት ዓመት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ሁለት ግራንድ ፕሮጀክቶች ላይ በርካታ ማኅበረሰብ ተኮር ተግባራት ማከናወኑን ገልጸዋል። በ2018 በጀት ዓመትም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ሥራ ማስቀጠልና ተጨማሪ ማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት