የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ ፈጠራ ልማት እና ማበልጸጊያ ማዕከል ከ ‹‹SNV RAYEE›› ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ለአርባ ምንጭ ከተማ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች የተዘጋጀውን የቢዝነስ ሃሳብ የመጨረሻ ዙር ውድድር ኅዳር 10/2016 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት የበለጸጉ የንግድ ሃሳቦችን ማቅረብ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ውድድሮች ተመራጭ ለመሆን ያግዛል፡፡ ውድድሩ ዘላቂ እንዲሆን አዳዲስ ሃሳቦችን ማፍለቅና ቴክኖሎጂዎችን ማዘመን ወሳኝ ነው ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ የተገኙ ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀምና ከሚታዩ ዓለም አቀፍ ለውጦች ጋር ራስን ማላመድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የሥራ ፈጠራ ልማት እና ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ ውድድሩ የከተማዋ ሥራ ፈጣሪዎችና ሃሳብ አፍላቂ ወጣቶች እንዲሁም ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሃሳባቸውን በማስገምገም እንዲያዳብሩ፣ ወደ መሬት ማውረድ እንዲችሉና ያለባቸውን የፋይናንስና የዕውቀት ክፍተት ለመሙላት እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ውድድሩ ከማስታወቂያ ጀምሮ ሦስት ሂደቶችን አልፎ እስከ ፍጻሜ እስኪደርስ ሂደቱ በዩኒቨርሲቲው በገለልተኝነት የተካሄደ ሲሆን የውድድሩ አሸናፊዎች የመነሻ የገንዘብ ሽልማት በፕሮጀክቱ የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡ ዶ/ር ወንድወሰን በትግበራ ሂደቱ ላይም የዩኒቨርሲቲው ክትትል፣ ሙያዊ እገዛና ድጋፍ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ - ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን በመደገፍና በማበረታታት ረገድ ማእከሉ አመርቂ ለውጦችን እያሳየ መምጣቱንና በቀጣይም ከተለያዩ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሥራቸውን ወደ መሬት ማውረድ እንዲችሉ ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የ‹‹SNV RAYEE›› ፕሮጀክት አርባ ምንጭ ክላስተር የወጣቶች ሥራ ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት አማካሪ አቶ አብነት ጴጥሮስ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተለያዩ ሥራዎችን በአጋርነት እንደሚሠሩ ጠቅሰው ፕሮጀክቱ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች በተለይም ሴቶችና በግብርና ዘርፍ ላይ የሚሰማሩ ወጣቶች ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ወጣቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ከባለድርሻ አካላት ጋር ማስተሳሰር ዋነኛ ዓላማቸው እንደሆነ የተናገሩት አማካሪው በውድድሩ ከ1 እስከ 3 ለወጡ አሸናፊዎች ሙሉ የሽልማቱ ወጪ በፕሮጀክቱ እንደሚሸፈን ገልጸዋል፡፡ የቀረቡት የሥራ ፈጠራ ሃሳቦች ችግር ፈቺና ወደ ገበያ ቢገቡ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚችሉና ይህም እንደ ሀገር ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑን አቶ አብነት ተናግረዋል፡፡ 

የውድድሩ ተሳታፊዎች ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ ሃሳቦችን የያዙ ወጣቶች በሃሳብም ሆነ በበጀት መደገፍ ከቻሉ ውጤታማ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡ ውድድሩ የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ያላቸው እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ ዕድል የሚፈጥርና ከገምጋሚዎች የተሰጡ ገንቢ አስተያየቶችም ለቀጣይ ሥራ እንደሚረዷቸው ተናግረዋል፡፡

በውድድሩ ፍጻሜ ከቀረቡ 7 የፈጠራ ሃሳቦች መካከል የእንስሳት መኖ ማምረት፣ ከአካባቢያችን በቀላሉ በሚገኙ ቁሳቁሶች የሚሠራ የጫጩት መፈልፈያና ለአረም መንቀያነት የሚውል ዘመናዊ ማሽን ተጠቃሽ ሲሆኑ በቀጣይ ከ1-3 የወጡ ተወዳዳሪዎች ውጤታቸው ተገልጾ የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው በመድረኩ ተገልጿል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት