አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ‹‹GIZ››፣ እፉዬ ገላ ኢቨንት ቴክኖሎጂና ኮንሰልተንሲ እና ኢትዮጆብስ ጋር በመተባበር ከኅዳር 22-26/2015 ዓ/ም በጫሞ ሐይቅ ዙሪያ ሀካቶን አካሂዷል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ሀካቶን በቡድን ችግሮችን ለመፍታት ወይም ፈጠራዎችን ለመፍጠር ከ2-5 ግለሰቦች የሚሰበሰቡበት ዓውደ ጥናት ሲሆን ዓላማው በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ የጽንሰ ሃሳብ ማረጋገጫ መፍጠር ነው ያሉት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ‹‹IUC›› ፕሮግራም ማኔጀር ዶ/ር ፋሲል እሸቱ ናቸው፡፡ በጫሞ ሐይቅ ችግሮች ዙሪያ ዘላቂ መፍትሄ ለመፈለግ በተለያዩ የትምህርትና የሥራ መስኮች የተሠማሩ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ተሳታፊዎቹ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማመንጨት ይረዳቸው ዘንድ የጫሞ ተፋሰስ ከዛሬ 100 ዓመታት በፊት ምን ይመስል እንደነበር፣ አሁን ምን ደረጃ ላይ እንዳለ፣ ሐይቁን በዘላቂነት መታደግ ካልተቻለ ወደፊት ምን ሊፈጠር እንደሚችልና ሌሎች የሐይቁ መሠረታዊ ችግሮችና ስጋቶች ላይ ሰፋ ያለ ገለጻ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ዶ/ር ፋሲል አክለውም ተሳታፊዎቹ የተለያዩ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው የጫሞ ተፋሰስ እንዲያገግም የሚያመጡት የመፍትሄ ሃሳብ ምን ያክል ከችግሩ ጋር ይቀራረባል የሚለው ተገምግሞ በተቀመጠለት መስፈርት መሠረት ተቀባይነት ካገኘ ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚደረግ ሲሆን እኛ ለምናደርገው ምርምርም ግብዓት ይሆናል ብለዋል፡፡

የመፍትሄ ፍለጋ ሂደቱ ተሳታፊዎች ወጣት እንደመሆናቸው ከተመራማሪዎች ጋር አብሮ የመሥራት እንዲሁም መፍትሔ የማምጣት ልምዳቸው እንደሚዳብር ዶ/ር ፋሲል ተናግረዋል፡፡ ከጫሞ ተፋሰስ ጋር በተያያዘ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር መሥራት ለሚፈልግ ማንኛውም ባለ ድርሻ አካል በራችን ክፍት ያሉት ዶ/ር ፋሲል ተፈጥሮን ለመታደግና ለመንከባከብ እኛ የመጨረሻ ትውልዶች በመሆናችን የምናባክነው ጊዜ እንደሌለ አውቀን ሁላችንም የድርሻችንን ብንወጣ ለውጥ ይመጣል ብለዋል፡፡

ከአርባ ምንጭ ሌቶ ሁለገብ አሳ አስጋሪዎች ማኅበር የመጡት ተሳታፊ አቶ አሰግድ ጮሎ በየደረጃው ያሉ የሚመለከታቸው አመራሮችና የአስተዳደር አካላት ጫሞ ሐይቅን ለመታደግ ትኩረት ሰጥተው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱና ሐይቁን እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከአዲስ አበባ የመጣችው ተሳታፊ ‹‹Learning Experience Designer›› ወ/ሪት ዲና ያዕቆብ በበኩሏ በጫሞ ሐይቅ ችግሮች ላይ የመፍትሄ ሃሳብ ለማፍለቅ ላለፉት ሦስት ቀናት እየሠሩ መቆየታቸውን ገልጻ ለመስክ ምልከታ ወደ ሐይቁ በሄድንበት ወቅት በሐይቁ ዙሪያ የባለቤትነት ስሜት አለመኖሩን አስተውለናል ብላለች፡፡ በቆይታቸው ስለሐይቁ ያገባኛል የሚሉ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች የሚሰባሰቡበትና ሐይቁን ለመታደግ በጋራ የሚሠሩበትን ፕላትፎርም እንደ መፍትሄ ማቅረባቸውንም ተናግራለች፡፡

ሌላኛው ተሳታፊ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ 4ኛ ዓመት ተማሪ ፍራኦል ሰሎሞን ከአንድ ዓመት በፊት ለትምህርት ላይ ልምምድ ወደ ጫሞ ሐይቅ በመጣበት ጊዜ ከነበረው ችግር የአሁኑ የከፋ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ተማሪ ፍራኦል በአካባቢው የተለያዩ የግብርና እንቅስቃሴዎች እንዲሁም የኢንቬስትመንት ፕሮጀክቶችን ማስተዋሉን ጠቅሶ ይህም ሐይቁን በእጅጉ እየጎዳው ነው ብሏል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከሐይቁ ጥቅም እያገኘ ሐይቁን ራሱ እንዲጠብቅና እንዲንከባከብ ለማድረግ ተደራሽ ሚዲያዎችን ተጠቅሞ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ሊሠራ ይገባል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

በኢኮኖሚክስ፣ በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ፣ በግብርና ትምህርት መስክ እንዲሁም በዓሳ ማጥመድ ሥራ ላይ የተሠማሩ 35 ተሳታፊዎች ከአዲስ አበባ፣ ሀዋሳና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከአርባ ምንጭ ከተማ የተወጣጡ ናቸው፡፡ በመፍትሄ ፍለጋ ሂደትም ብራይት፣ ባይራ፣ ኦክቶፐስ፣ ዜብራ፣ ዱቡሻ እና ፋይንድ ኢት የሚሉ የቡድን መጠሪያዎችን የተጠቀሙ ሲሆን ባመጡት የመፍትሄ ሃሳብ መሠረት ባይራ የ1ኛ፣ ፋይንድ ኢት 2ኛ እና ዱቡሻ 3ኛ ደረጃን አግኝተው እንደየደረጃቸው 2,000፣ 1,500 እና 1,000 ዩሮ የሥራ ማስኬጃ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚበረከትላቸው ተገልጿል፡፡ በፕሮግራሙ ፍፃሜ ለተሳታፊዎች የተሳትፎ የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት