የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጫሞ ካምፓስ በ2017 በጀት ዓመት በምርምር ኅትመት እና ግራንት ፕሮጀክቶችን በማሸነፍ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተመራማሪዎች እና መምህራን ጥቅምት 15/2018 ዓ/ም ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የፕብሊኬሽን ሥራን በማሳደግ የምናገኛቸውን ግብዓቶች በማቀናጀት ለሥራ ማዋልና ማኅበረሰቡን ማገልገል እንዲሁም በትብብር ከማኅበረሰቡ ጋር መሥራት ዋነኛ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መርሐ ግብሩም በትጋት የሠሩትን የበለጠ ለማበረታታት እንዲሁም የማመስገን ባህልን ለማዳበር እንደሚረዳ ዶ/ር ተስፋዬ ገልጸው ተነሳሽነት ኖሮ ግራንቶችን ለማምጣት እና የምርምር ሥራዎችን በስፋት ለማሳተም እንድንችል ያግዛል ብለዋል፡፡ መሰል መድረኮች ሊለመዱ እንደሚገባ እንዲሁም በየኮሌጁና ትምህርት ክፍሎችም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ዶ/ር ተስፋዬ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ 

የሥነ ትምህርትና ሥነ ባሕርይ ሳይንስ ት/ቤት ዲንና የካምፓሱ ኃላፊ አቶ አንለይ ብርሃኑ መርሐ ግብሩ በካምፓሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰናዳ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ተመራማሪዎቹን የበለጠ የሚያተጋ እና ለሌሎች መምህራን አርአያ ሆነው አቅጣጫዎችን የሚያሳዩበት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መርሐ ግብሩ በካምፓስ ደረጃ ሲካሄድ ከሽልማት ባሻገር የትብብር ሥራን በማጎልበት በመማር ማስተማር፣ በምርምር እንዲሁም በግራንት ፕሮጀክት ላይ በጋራ መሥራት የሚያስችል መሠረት የሚጥል መሆኑን የተናገሩት አቶ አንለይ የምርምር ኅትመቶችን ለማሳደግ እንዲሁም ትላልቅ ግራንት ፕሮጀክቶችን ለማሸነፍ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

የኅትመት ሥርጭትና ስነዳ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ስምዖን ደርኬ በምርምር ኅትመትና ግራንት ማኔጅመንት አሁናዊ መረጃዎች ላይ ሰፋ ያለ ገለጻ በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይም የሚሠሩ የምርምር ኅትመት ቁጥሮችን መጨመር እንደሚገባ አቅጣጫዎችንም አመላክተዋል፡፡

በዕውቅና አሰጣጡ በዓመቱ ምርጥ ምርምር አሳታሚ(Best Publisher) ከማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ ከ1-3ኛ ዶ/ር አበራ ኡንቻ፣ ዶ/ር ኃይላይ ተስፋዬና ዶ/ር የቻለ ከበደ፣ ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ አቶ ዳመነ ቦጋለ፣ ዶ/ር መልካሙ ማዳ፣ ዶ/ር ማሌቦ ማንቻ፣ ከሥነ ትምህርትና ሥነ ባሕርይ ሳይንስ ኮሌጅ ዶ/ር ሙልቀን ተስፋዬ፣ ከሕግ ትምህርት ቤት Dr.Prem Sam Ponniah Victor ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

በምርጥ የግራንት ፕሮጀክት አሸናፊ ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ ከማኅበራዊ ሳይነስና ስነ ሰብ ኮሌጅ ከፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ዶ/ር ይሄነው ውቡ ዕውቅና ተበርክቶላቸዋል፡፡

ከተሸላሚዎች መካከል የዓመቱ ምርጥ የግራንት ፕሮጀክት ዘርፍ አሸናፊ የሆኑት ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ በሽልማቱ መደሰታቸውን ገልጸው ስኬቱ የጋራ ትብብር ውጤት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መልካም አጋጣሚን መጠቀም፣ አዋዋልን ማሳመር እንዲሁም ጠቃሚ የሆኑ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን መከተል እንደሚገባ ከተሞክሯቸው አጋርተዋል፡፡ 

የጉባኤው ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየት መሰል መድረኮች ተሳታፊዎችን ለምርምር ሥራ የሚያነቃቃና  የሚያነሣሣ መሆኑን ገልጸው ጥሩ ልምድና ተሞክሮ ለመቀመር አጋዥ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት