የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ማስትሪች የተሰኘ የኔዝርላንድ ዩኒቨርሲቲ በጎ ፈቃደኛ ተማሪዎች ባሰባሰቡት ገንዘብ  በጫሞ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ ለሚገኘው የልዩ ፍላጎት ት/ቤት እድሳትና የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ኅዳር 17/2016 ዓ.ም አድርጓል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ አካዳሚክ ዳይሬክተር አቶ በላይ ቦዳ ከመማር ማስተማርና ምርምር ሥራዎች ባሻገር ኮሌጁ የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎችን እንደሚያከናውን ጠቅሰዋል፡፡ በበጎ ፈቃደኛ ተማሪዎቹና በኮሌጁ ትብብር የተሰራው ሥራ አበረታች መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ በኮሌጁ በሚገኙ እንደ ልማታዊ ቡድን ሥልጠና( Developmental Team Training Program)  ባሉ ፕሮግራሞች ለት/ቤቱ ተጨማሪ ድጋፎችን ለማድረግ ይሰራል ብለዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሪት ገሊላ ቢረሳው የልዩ ፍላጎት ትምህርት ከመደበኛ ትምህርት አንጻር በሃገሪቱ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ አለመሆኑንና በርካታ ችግሮች በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለትምህርት ቤቱ የተደረገው ድጋፍ የትምህርት ቤቱን የመማር ማስተማር ሂደት የሚያሻሽል መሆኑን የገለጹት ወ/ሪት ገሊላ መማሪያ ክፍሉን ከማደስና ምቹ ከማድረግ ባሻገር ቦርሳ፣ ደብተር፣ እርሳስ፣ እስክሪብቶ፣ የሙዚቃ ማሳሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ለሥራው አጋዥ የሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል፡፡

የበጎ አድራጎት ሥራው አስተባባሪ Miss Anouk Mommers በበኩሏ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ የመሳተፍ ሕልም እንደነበራት ተናግራ ድጋፉ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር የተሰራ መሆኑን ተናግራለች፡፡ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎችን የምናስተምርበት መንገድ የተለየ ሊሆን እንደሚገባና ለት/ቤቱ የተደረገው ድጋፍ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲማሩ የሚያግዝ መሆኑንም ጠቁማለች፡፡

የአርባ ምንጭ የልዩ ፍላጎት ት/ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ታዲዮስ ፈጠነ ከዚህ ቀደም የመማሪያ ክፍሉ ለተማሪዎች ምቹ ካለመሆኑ ባሻገር በቁሳቁስም የተሟላ እንዳልነበር ጠቁመዋል፡፡ ከክፍል ጥገና ጀምሮ ክፍሉን በማስዋብና አስፈላጊ መርጃ መሳሪያዎችን ማሟላት በመቻሉ የመማሪያ ስፍራውን ለተማሪዎች ምቹ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ለዚህም ርዕሰ መምህሩ በሥራው ላይ ለተሳተፉ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ መሰል ትምህርት ቤት በሲቀላም እንዳለ አቶ ታዲዮስ ጠቅሰው በቂ መርጃ መሳሪያ የሌላቸውና መማሪያ ክፍሎችም ምቹ እንዳልሆኑ በመግለጽ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እንዲሁም ማኅበረሰቡ ቅንጅት ፈጥሮ ለት/ቤቶቹ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመርሃ ግበሩ ማጠቃለያ ላይ በበጎ ሥራው ለተሳተፉ ባለድርሻ አካላትና ግለሰቦች የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት