የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከተለያዩ ክልሎች ለተወጣጡና የወባ ፕሮግራምን ለሚያስተባብሩ የጤና ባለሙያዎች ከግንቦት 05 - ሰኔ 05/2016 ዓ/ም ለአንድ ወር የቆየ የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ላይ ያተኮረ (Comprehensive Malariology) ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የወባ ምርመራና ሕክምና፣ የማኅበረሰቡን የወባ በሽታ የመከላከያ ዘዴዎች አጠቃቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ አሰጣጦች፣ በወባ በሽታ ላይ የአመራሩ ዕቅድና አተገባበር እና ሌሎችም ርእሰ ጉዳዮች በሥልጠናው ተዳስሰዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር ‹‹National Malaria & Other Vector Borne Diseases Senior Expert›› አቶ ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት ከኮሌጁ ጋር ባለው የጋራ መግባቢያ ስምምነት መሠረት ሥልጠናው የተዘጋጀ ሲሆን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የወባ በሽታ ላቦራቶሪ መኖሩ እንዲሁም በአካባቢው የውኃ አካላት የሚገኙ መሆኑ ለተግባር ልምምድ አመቺ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ሠልጣኞች የመጡባቸው አካባቢዎች  ከፍተኛ የወባ ጫናና ስርጭት ያለባቸው በመሆኑ የዘርፉን ባለሙያዎች በሥልጠና በመደገፍ ያላቸውን ዕውቀትና ክሂሎት በማሳደግ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ታልሞ መሠልጠናቸውንም ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ጥላሁን የወባ በሽታ በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች አማካኝነት እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን ቀጣዩ ዝናባማ የክረምት ወቅት የወባ ስርጭት የሚስፋፋበት በመሆኑ ሥልጠናው ችግሩን ለመቀነስና ስርጭቱን ለመግታት ያግዛል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም ሕመምተኞችን ለማከም እንደ ሀገር በርካታ ሥራ የተሠራ ቢሆንም የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ለማስመዝገብ በየጤና ተቋማት ያሉ ባለሙያዎችን በማሠልጠን ንቁ ተሳታፊ ሆነው ሂደቱን እንዲደግፉ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በኮሌጁ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ማዕከል ማስ/ጽ/ቤት ኃላፊ ተ/ፕ ፈለቀ ገ/መስቀል  በኮሌጁ ከተለያዩ አጋር ተቋማት ጋር በመቀናጀት በጤናው ዘርፍ የክሂሎት ማዳበሪያ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡ በወባ መከላከልና መቆጣጠር ላይ በተሰጠው ሥልጠና መሠረት ሠልጣኞች ተግባር ላይ ማዋላቸውን ተቋሙ ከክልሉ ጋር በመቀናጀት የክትትል ሥራ እንደሚሠራ ተ/ፕ ፈለቀ ተናግረዋል፡፡

ከምዕራብ አርሲ የመጡት የሥልጠናው ተሳታፊ አቶ ደደሆ ማማ ወባን የመከላከልና የአስተዳደር ሂደቶችን ጨምሮ በወባ ዙሪያ ዕውቀትና ክሂሎታቸውን ማዳበራቸውን ተናግረው ከሥልጠናው ያገኙትን ልምድ ከታች ላሉ ባለሙያዎች በማውረድ ወባን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ከአዳማ የመጡት ሌላኛዋ ሠልጣኝ ትዕግሥት ተሾመ ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያግዝ ተግባራዊ ዕውቀት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በሥልጠናው ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ኦሮሚያ እና ሲዳማ ክልሎች የተወጣጡ 54 ተጠሪ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በሥልጠናው ማጠናቀቂያ የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በቀጣይ በ2 ዙር ሥልጠና ለአማራ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ባለሙያዎች የሚሰጥ ይሆናል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት