የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ሥልጠናና ምርምር ማዕከል በስትራቴጂያዊ ዕቅድ አፈጻጸምና በቀጣይ ዕቅዶች ላይ ጳጉሜ 03/2016 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ለሀገሪቱ የጤና ሥርዓት መሻሻል ማዕከሉ አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን ገልጸው ማዕከሉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት በኃይሉ መርደኪዮስ (ተ/ባ ፕ/ር) ዩኒቨርሲቲው በጤናው ዘርፍ በተለይም የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች የሥልጠናና ምርምር ማዕከል ከፍቶ ባከናወናቸው ተግባራት ከጤና ሚኒስቴር ዕውቅና የተሰጠውና ሌሎች ተቋማት ተሞክሮ የሚወስዱበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የምርምር ልምዶችን በመቅሰምና የምርምር ሥራን ሊያሳልጡ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት መሥራት እንደሚገባ ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ እንደገለጹት ከሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት ተሞክሮዎችን መቅሰም፣ የሚከናወኑ ተግባራትን በመረጃ ሰንዶ ማስቀመጥ እንዲሁም በማዕከሉ በምርምርና በጤናው ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራት ተደራሽ እንዲሆኑ ሚዲያን በአግባቡ መጠቀም ይገባል፡፡

የማዕከሉ ዳይሬክተር አብነት ገ/መስቀል (ረ/ፕ) እንደገለጹት በፈጠራ የታገዘ ምርምር ማካሄድ፣ ለጤና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎችን መከላከል የሚያስችል የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር ጠንካራ ትስስር መፍጠር በምርምር ማዕከሉ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በ‹‹Oxford Policy Management Country Strategic Adviser›› የሆኑት ዶ/ር አያና የኔአባት የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ካላቸው የተላላፊነት ባህርይ አንጻር ዓለም አቀፋዊ ትኩረት የሚሹ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ ዶ/ር አያና በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ከማኅበረሰቡ ጋር ጠንካራ ትስስር በመፍጠር ለቆላማ በሽታዎች ስርጭት መንስኤ በሆኑት ንጹሕ የመጠጥ ውኃና አካባቢ ንጽሕና ላይ በቂና ተግባር ተኮር የምርምር ሥራዎችን መሥራት፣ በበሽታዎቹ ላይ ያተኮረ ዘላቂ ሥርዓተ ትምህርት መቅረጽ እንዲሁም በበሽታዎቹ ዙሪያ የተዛቡ አመለካከቶችን መቀየር የሚያስችል የሚዲያ ስትራቴጂ መንደፍ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው፡፡

በ‹‹African International Trachoma Initiative Regional Director›› ዶ/ር ተሾመ ገብሬ የዓለም ጤና ድርጅት ከጤና ጋር በተያያዘ በአጋርነት ለሚሠሩ ተቋማት ድጋፍ እንደሚያደርግና የድርጅቱን መስፈርት ለሚያሟሉ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና የሚሰጥ ተቋም መሆኑን ጠቁመው ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ዘርፈ ብዙ የምርምር ተግባራትን ማካሄድ፣ የተለያዩ የኅትመት ሥራዎችን መሥራት እንዲሁም ጠንካራ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ስትራቴጂ መፍጠር በዓለም የጤና ድርጅት በኩል ዕውቅና ለማግኘት ከሚያስችሉ መስፈርቶች መካከል ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት