የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጤና ትምህርት ክፍል ‹‹Improving Post - Caesarean Breastfeeding via Lactation Midwives in Southern Ethiopia: A Randomized Controlled Trial›› በሚል ርእስ የትብብር ምርምር ግራንት ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ውይይት ሐምሌ 20/2016 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት በኃይሉ መርደኪዮስ (ተባባሪ ፕ/ር) በቀዶ ጥገና የሚወልዱ እናቶች ጡት ማጥባት የመጀመር አቅማቸውን የሚያዳክም ልዩ ፈተና እንደሚገጥማቸው ተናግረው ፕሮጀክቱ የሠለጠኑ የጡት ማጥባት ሚድዋይፎችን ዕውቀት በማጎልበት ችግሮቹን ለመፍታት የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ም/ፕሬዝደንቱ ይህ ፕሮጀክት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የእናቶችንና ሕፃናትን ጤና ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ትልቅ እመርታ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጤና ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ የሆኑት የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር መቅደስ ቆንዳሌ የምርምር ፕሮጀክቱ በቀዶ ጥገና የሚወልዱ እናቶች ከወለዱ በኋላ ከ30 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ሕፃናትን ባለማጥባታቸው ምክንያት በእናቶችና በሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ችግር ለመቅረፍ ታቅዶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ እንደ ዶ/ር መቅደስ በቀዶ ጥገና ወልደው በሳይንስ የተደገፈ የጡት ማጥባት ምክር የወሰዱ እናቶችን በጥናቱ በማካተት ተሞክሮዎቻቸውን ለሌሎች እናቶች እንዲያካፍሉ በማድረግ ጥሩ ውጤት ካሳየ በክልልና በሀገር ደረጃ ችግሩን ለመቅረፍ የሚሠራ ይሆናል፡፡

የኮሌጁ የጥናትና ምርምር ኮርፖሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዘርይሁን ዘርዶ በውይይቱ ለፕሮጀክቱ ስኬት የሚረዱና መካተት የሚገባቸው ገንቢ ሃሳቦች ከባለሙያዎች መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ 

የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ የእናቶችና የሕፃናት የሥነ ምግብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አጥናፉ አበራ በፕሮጀክቱ መጀመር የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ሲጠናቀቅ ከቀዶ ጥገና በኋላ እናቶች ልጆቻቸውን ጡት ከማጥባት ጋር የሚነሱ ችግሮችን በሚቀርፍ ሁኔታ እንዲሠራ አሳስበው መምሪያው ለፕሮጀክቱ ስኬት አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግና በጋራ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡


አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት