የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ  ትምህርት ቤት የ2017 ዓ/ም ትምህርት ዘመን ማጠናቀቂያ፣ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ምረቃ፣ የተማሪ ወላጆች ቀንና የውጤት ማሳወቂያ መርሐ ግብር ሐምሌ 12/2017 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ትምህርት ለአንድ ሀገር ዕድገትና ሁለንተናዊ ለውጥ ቁልፍ መሳሪያ በመሆኑ ትምህርቱ በሁሉም እርከን በተገቢው ሊመራ ይገባል ብለዋል። አያይዘውም በተማሪዎች አፈጻጸም ውስጥ የወላጆች ሚና ከፍተኛ እና ዘርፈ ብዙ ነው ያሉት ዶ/ር ተክሉ አዎንታዊ የወላጅ ተሳትፎ ከፍተኛ የትምህርት ውጤትን፣ የተሻለ ባህሪን እና የማህበራዊ ክህሎቶችን እንደሚጨምር ጠቁመዋል። በመሆኑ ወላጆች በልጆቻቸው ትምህርት በንቃት በመሳተፍ እና ድጋፍ እና ግብዓቶችን በመስጠት የህይወት ዘመን የመማር ጉዞ ጠንካራ መሰረት እንዲፈጥሩ ዶ/ር ተክሉ  አሳስበዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝትና ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ  ለቅድመ መደበኛ ተመራቂ ተማሪዎችን እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።  የትምህርት ዘመኑ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ብዙ ነገር የተማርንበት ነው ያሉት ዶ/ር ቶሌራ  ተግዳሮቶች ቢገጥሙንም ስኬቶችን በጋራ ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል። የትምህርት ሥራ  ትልቅና ሰፊ ነው ያሉት ዶ/ር ቶሌራ ውጤታማ የትምህርት ሥርዓት ለመፍጠር ከከዚህ ቀደሙ በተሻለ መንገድ ሁሉም ባለድረሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። ዶ/ር ቶሌራ የትምህርት ዘመኑ በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ ለተወጡ የት/ቤቱ ማኅበረሰብ በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ስላስ ጎዳና እንደገለጹት በ1990 ዓ/ም የተቋቋመው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ አጸደ ህጻናት ትምህርት ቤት ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት ለ28 ዙሮች ህጻናትን በአጥጋቢ ውጤት አብቅቶ ለመደበኛ ትምህርት አብቅቷል፡፡ ሥራ አስኪያጁ  በ2017 ትምህርት ዘመን የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮችና በ2018 ዓ/ም ትኩረት የሚደረግባቸው ቁልፍ ተግባራት ላይ ዝርዝር ሀሳቦችን በዕለቱ አቅርበዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ተመራቂ ተማሪዎች የተለያዩ ሥነ-ጽሑፎችንና ትምህርታዊ ውድድሮችን ለታዳሚዎች ያቀረቡ ሲሆን ከየክፍሉ ከ1-3 ለወጡ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማትም ተሰጥቷል፡፡


ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት