የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት የ2018 ዓ/ም የመጀመሪያው የመምህራን የጋራ ጉባኤ ጥቅምት 14/2018 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
ጉባኤው በተለይም ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ የ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት መሻሻል ላይ ያተኮረ ሲሆን ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ማዘጋጀትና መምህራን ቅጥር ማካሄድ በውይይቱ የተካተቱ ጉዳዮች ናቸው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በለውጥ ጎዳና ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ ከመምህራኑ ብዙ የሚጠበቅ መሆኑን ጠቅሰው ተማሪዎችን በብቃት ማዘጋጀት እንዲሁም ተቋሙን ውጤታማ እና ተመራጭ እንዲሆን መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገ/ማሪያም ትምህርት ቤት ትውልድ የሚቀረጽበት እንደመሆኑ መንግሥት ያስቀመጠውን አቅጣጫ በመከተል ከታችኛው ደረጃ ጀምሮ በጥራት ለማብቃት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ሀገራዊ አቅጣጫውን በመረዳት ከሪፎርሙ ጋር ራስን ማስማማት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው መምህራን ተማሪዎችን እንደየአቀባበላቸው ለይተው መከታተልና መርዳት ብሎም ከጊዜው ጋር ራስን ማዘመን አለባቸው ብለዋል፡፡
የማኅበረሰብ ጉድኝትና ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ በዚህ ዓመት ትምህርት ቤቱን ለመቀየር ሪፎርም እየተደረገ በመሆኑ በጋራ ያቀድነውን ዕቅድ ለማሳካት የመምህራን ተነሳሽነት ትልቅ ድረሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሥላስ ጎዳና በ2017 የትምህርት ዘመን የተከናወኑ ተግባራት እና ያጋጠሙ ችግሮች፣ በ2018 ዓ/ም ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች፣ የ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል የውጤት መሻሻል እና አተገባበር ዙሪያ ዝርዝር ሃሳቦችን በውይይቱ አቅርበዋል፡፡
መንግሥት ያስቀመጠውን የሪፎርም አጀንዳ ለማስቀጠል ሥራዎችን በማዘመን ቀላል፣ ውጤታማ እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ መሥራት፣ የሥራ አካባቢን ምቹ በማድረግ መምህራን የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት እንዲችሉ ማድረግ እንዲሁም አመለካከቶችን እና አሠራሮችን በመለወጥ ከሌሎች ተቋማት ጋር ተፎካካሪ በመሆን ትምህርት ቤታችንን ተመራጭ እንዲሆን ለማድረግ እያንዳንዱ መምህር ግዴታ እንዳለበት አቶ ሥላስ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የጉባኤው ተሳታፊዎች በአስተያየታቸው መምህራን ይበልጥ ተቀራርቦ በመደጋገፍ የመሥራት ባህልን ቢያዳብሩ ውጤታማ ለመሆን እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የተሻለ ለሚሠሩ መምህራን የማበረታቻ ዕውቅና ቢሰጥ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

