የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ትምህርትና ሥነ ባሕርይ ሳይንስ ት/ቤት የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ለኮሚዩኒቲ 1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ‹‹የመማር ማስተማር ሥነ ዘዴ እና ጤናማ ተግባቦት ጤናማ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር›› በሚል ርእስ ከጥቅምት 21-23/2017 ዓ/ም የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሥነ ትምህርትና ሥነ ባሕርይ ሳይንስ ት/ቤት የማኅበረሰብ ጉድኝት አስተባባሪ መ/ርት ውድነሽ አስጨናቂ ሥልጠናው በዋናነት የመማር ማስተማር ሥነ ዘዴ እና ጤናማ ተግባቦት ጤናማ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር ያለው ጠቀሜታ ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አስተባባሪዋ የተማሪን ውጤት ለማሻሻል መምህሩ ዕውቀት የሚያስተላፍበት መንገድ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም ጤናማ ተግባቦት ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡ 

የሥነ ትምህርትና ሥነ ባሕርይ ሳይንስ ት/ቤት የሥነ ትምህርት ት/ክፍል ተጠሪ ተወካይ ዶ/ር ዘላለም ዘካሪያስ እንደገለጹት ሥልጠናው መምህራን በሚያስተምሩት የትምህርት ዓይነት ላይ ብቻ ሳይሆን ትምህርቱን በሚያስተላልፉበት መንገድ ላይ የተሻለ ዕውቀት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻልና ውጤታማ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲኖር ሥልጠናው ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ዶ/ር ዘላለም ተናግረዋል፡፡ 

የሥነ ትምህርትና ሥነ ባሕርይ ሳይንስ ት/ቤት መምህር የሆኑት አሠልጣኝ ዶ/ር ድጋፌ ዳርዛ ሥርዓተ ትምህርትና የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ፣ የተማሪ አያያዝ፣ የማስተማሪያ ሥነ ዘዴ እና የመማር ማስተማር ሁኔታን በክፍል ውስጥ መከታተል ላይ ክፍተቶችን ለመሙላት ሥልጠና መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች ሥልጠናው የመምህራንን የመማር ማስተማር ዕውቀትና ክሂሎት የሚያዳብርና አዳዲስ ዕውቀትና ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡


አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት