የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት የ2016 ዓ/ም ትምህርት ሥራ ማጠናቀቂያ የወላጅ ቀን በዓል ለአጸደ ሕጻናት ሰኔ 23 እና ለአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ሰኔ 30/2016 ዓ/ም ተከብሯል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በ2016 የትምህርት ዘመን ማጠቃለያ የወላጆች ቀን በዓል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት እንደ ተቋም ከፍተኛ የሆነ የመማር ማስተማር ሥራ በተሻለ ደረጃ እያከናወነ እንደሚገኝ በመጥቀስ ትምህርት ቤቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ውጤት በዞን ደረጃ አንደኛ ደረጃ ላይ መሆኑን ፕሬዝደንቱ አውስተዋል፡፡ በቀጣይም የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲቻል ተማሪዎች በክረምት ጊዜያቸው መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን እንዲያነቡ ወላጆች በቅርበት መከታተል እንደሚገባቸው እንዲሁም አንድ መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ የሚለውን ክልላዊ መሪ ቃል ተግባራዊ ለማድረግ እንደ ት/ቤት ግንባር ቀደም ለመሆን ሊሠራ እንደሚገባ ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት ለተማሪው ስኬት ወላጆች ያላቸው ሚና ከፍተኛ ስለሆነ ወላጆች ልጆቻቸውን በቃላቸው፣ በተግባራቸው፣ በፍቅራቸው አርአያ ሆነው እየቀረጹ ማሳደግ ይኖርባቸዋል፡፡ ትምህርት ጥራቱ እንዲጠበቅ የሚያስፈልገውን ግብዓት ሁሉ አሟልቶ መሄድ የሚገባ በመሆኑ በሀገራችን የሚታየው የትምህርት ስብራት እንዲጠገን እንደ ሀገር የተጀመረው የትምህርት ፖሊሲ ከታች ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ አቅጣጫ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና የትምህርት ቤቱ ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደተናገሩት ሕጻናት ከዕድሜያቸው አንጻር ልዩ እንክብካቤ ሊደረግላቸው ያስፈልጋል፡፡ በሰው ልጅ እድገት ላይ በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት መሠረት መጣል ስላለበት ወላጆች አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባቸው ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ስላስ ጎዳና እንደገለጹት በ1990 ዓ/ም የተቋቋመው የኮሚዩኒቲ ት/ቤት አጸደ ሕጻናት ትምህርት ቤት ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት በ27 ዙር ሕጻናትን በአጥጋቢ ውጤት አብቅቶ በማስመረቅ ለመደበኛው ትምህርት ቤት ማስረከቡን ገልጸዋል፡፡ በዚህም በርካታ ባለሙያዎችን በተለያዩ የሥራ መስኮች ያፈራ ትምህርት ቤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ ስላስ የአጸደ ሕጻናት የትምህርት ደረጃ የሚፈልገው ግብዓት፣ ጊዜና የሰው ኃያል ትኩረት ከፍተኛ ስለሆነ ሁሉም ወላጆች የየራሳቸውን ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው አሳስበዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ አጸደ ሕጻናት ትምህርት ቤት ር/መምህርት ሳራ ጎይዳ በበኩላቸው ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ዋነኛ መገለጫው በአጸደ ሕጻናት ትምህርት አሰጣጥ በሠለጠኑ ባለሙያዎች የሚሰጥ የትምህርት ደረጃ ሲሆን በዚህም ሕጻናት ከሌሎች ጋር አብሮ መሥራትን ይማራሉ፤ ጓደኝነትን ይመሠርታሉ፤ በኅብረት ይጫወታሉ፤ የፈጠራ ችሎታቸውን በውዝዋዜና በእንቅስቃሴ ይገልጻሉ፤ ከመምህራንና ሌሎች ሰዎች ጋር በሚያደርጉት መደማመጥና ጭውውት የተግባቦት ክሂሎታቸውን ያዳብራሉ፤ የንባብ፣ የመጻፍና የማስላት ክሂሎታቸውንም ያዳብራሉ ብለዋል፡፡ እንዲሁም በ2016 ዓ/ም የትምህርት ዘመን ወንድ 201፣ ሴት 198 በድምር 399 የአጸደ ሕጻናት ተማሪዎችን ተቀብሎ በዘርፉ ባለሙያዎች በመታገዝ የዓመቱን ሥራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ር/መምህር አቶ ካሳሁን ዲጤ እንደገለጹት እንደ ሀገር መንግሥት የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በትኩረት እየሠራ የሚገኝ ሲሆን የትምህርት ተደራሽነትን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ በማስተማር የተማሪዎች ውጤትን ማሻሻል ቁልፍ ጉዳይ አድርጎ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ ስለዚህ ትምህርት ቤቱም በ2025 በትምህርት ውጤት ልቀው የሚታዩና በሥነ ምግባራቸው ምስጉን የሆኑ ተማሪዎች መፍለቂያ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት በትጋት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ተማሪዎች የተለያዩ ሥነ-ጽሑፎችንና ትምህርታዊ ውድድሮችን ለታዳሚ አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም ከየክፍሉ ከ1-3 ለወጡ ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቷል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት