አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2017 በጀት ዓመት የተከናወኑ የማኅበረሰብ ጉድኝት ተግባራትን ለማኅበረሰቡና ለባለድርሻዎች የሚያስተዋውቅበትና ለቀጣይ ዕቅዶች የጋራ አቅጣጫ የሚይዝበት ዓመታዊ የማኅበረሰብና የሳይንስ ቀን ለ9ኛ ጊዜ ከኅዳር 25 – 26/2018 ዓ/ም ይካሄዳል፡፡
በመርሐ ግብሩ የ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች በሳይንስ ዙሪያ የጥያቄና መልስ ውድድር፣ በወቅታዊ የሳይንስና የማኅበረሰብ ትብብር ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት እና ኤግዚቢሽን እንዲሁም በየካምፓስ የተዘጋጁ የሳይንስ ፕሮግራሞች፣ የቤተ-ሙከራዎችና ወርክሾፖች ጉብኝት የሚደረግ ይሆናል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ አገልግሎት ተልዕኮው ላይ የማኅበረሰብ ግንዛቤና ተሳትፎ ለማሳደግ ዓመታዊ የማኅበረሰብና የሳይንስ ቀን ማክበር ከጀመረ 8 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ከማኅበረሰቡ እና በምርምር ትብብር ከሚመጡ የተለያዩ አጋዥ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በመተባበር የገጠር ት/ቤቶችንና ጤና አጠባበቅ ጣቢያዎችን በፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ከማድረግ እስከ የገጠር ቀበሌ በመካከለኛ የሐይድሮፓወር ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እስከ ማድረግ፣ ቀደም ብለው የተሠሩ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን ከመጠገንና ከማስፋፋት እስከ ሙሉ በሙሉ ምንጭ አጎልብቶ ጥቅም ላይ እስከ ማዋል፣ የውኃ ካልቨርቶችንና ድልድዮችን ከመገንበት እስከ አነስተኛ አገናኝ መንገድ እስከ መክፈት፣ የግብርና ችግሮችን ከመቅረፍ፣ የከተማ-ገጠር ትስስር ከመፍጠርና አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ከማስተዋወቅ እስከ ምርታማነትንና የገበያ ዕሴት ሠንሰለትን እስከ ማሳደግ እና ዘርፈ ብዙ የማማከር አገልግሎቶችን ጨምሮ አመርቂ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተሰጡትን የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማኅበረሰብ ጉድኝት ዐበይት ተልዕኮዎችን በብቃትና በጥራት እየተወጣ ለአራት አሥርት ዓመታት ያለመታከት ሩቅ አልሞና አቅዶ በመጓዝ ላይ ያለ አንጋፋ ተቋም ነው፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

