የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሁሉ አቀፍ ሴክተር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በአርባ ምንጭ ከተማ ለሚገኙ ለሁለት መቶ አካል ጉዳተኛ፣ ወላጅ አልባና አቅመ ደካማ ተማሪዎች መስከረም 21/2017 ዓ/ም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት በአብዛኛው የትምህርት ዘመን ጅማሬ ወቅት አቅም ለሌላቸው ወላጆች አስቸጋሪ ጊዜ በመሆኑ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይርቁ የሚያስችሉ ድጋፎችን ማድረግ ይገባል፡፡ እንደ ሀገር አሁን ላይ እየተጠናከረ የመጣው እርስ በእርስ የመደጋገፍና መተጋገዝ ልማዳን የማጠናከር ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ፕሬዝደንቱ በንግግራቸው አውስተዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊና ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ጌታቸው በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም በከተማው ለሚገኙ ድጋፍ ለሚሹ አካላት ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡ በዛሬው ዕለትም ዩኒቨርሲቲው በከተማው ለሚገኙ አቅመ ደካማ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላደረገው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሁሉ አቀፍ ሴክተር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መርክነህ መኩሪያ ዳይሬክቶሬቱ በየዓመቱ በዕቅድ ከሚሰራቸው ሥራወች አንዱ አካል ጉዳተኛ፣ ወላጅ አጥ፣ ተጋላጭና አቅመ ደካማ ለሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ መሆኑን ጠቁመው ዘንድሮም ለሁለት መቶ ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው 12 ደብተርና 10 አስክሪፕቶ ድጋፍ የተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የድጋፉ ተጠቃሚ የሆኑት የጋንታ በር ቀበሌ ነዋሪ ወ/ሮ መቅደስ ሻንቆ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ አስፈላጊውን ቁሳቁስ አሟልቶ ልጅን ማስተማር ፈታኝ መሆኑን ተናግረው የተደረገው ድጋፍ ልጆቻችን ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ በአግባቡ እንዲከታተሉ የሚያደረግ ነው ብለዋል፡፡

 

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት