የዩኒቨርሲቲው ተቋማዊ ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት በዩኒቨርሲቲው የበለጸገ ‹‹Curriculum Monitoring Dashboard›› በተሰኘ የሥርዓተ ትምህርት መከታተያ ሶፍትዌር አጠቃቀምን አስመልክቶ ለቴክኖሎጂ እና ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ፋከልቲ ዲኖች፣ ሳይንትፊክ ዳይሬክተሮች፣ ፋከልቲ ተጠሪዎችና ለተቋማዊ ጥራት ማረጋገጫ አስተባባሪዎች ጥቅምት 20/2018 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንትፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ እና ወደ ራስ ገዝነት ጉዞ ላይ ያለ እንደመሆኑ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ትልቅ ትኩረቱ ነው፡፡ በመሆኑም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሥርዓተ ትምህርትን ለመከታተል የሚረዳው ይህ ሶፍትዌር ጥራት ያለው ትምህርት ለተማሪዎች ለመስጠት የሚረዳና ወደፊትም የዩኒቨርሲቲውን ተመራጭነት የሚያሳድግ ነው ብለዋል፡፡

የተቋማዊ ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ኤፍሬም ጌታሁን በበኩላቸው እንደ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራ ጥራትን ለማሳደግ፣ በተያዘለት ጊዜ እንዲተገበር ለማስቻል እና ከተለምዷዊ አሠራሮች ለመውጣት ሶፍትዌሩ በመልጸጉን ገልጸው ሥልጠናው በሶፍትዌሩ አጠቃቀም ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ኤፍሬም ሶፍትዌሩ መምህራን የተሰጣቸውን የትምህርት ክፍለ ጊዜ በአግባቡ እንዲጠቀሙ፣ ተማሪዎች በአግባቡ እንዲማሩ  በመርዳት የመማር ማስተማር ሂደትን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርስ ነው፡፡ ሶፍትዌሩ በዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተዘጋጀ ሲሆን በኮሌጁ ተሞክሮ ውጤታማ በመሆኑ በሌሎች የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች ተግባራዊ እንዲሆን ታልሞ ሥልጠናው መሰጠቱን አስረድተዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የትምህርት ጥራት ዳይሬክተር ረ/ፕ አብነት ተሾመ እንደገለጹት ሶፍትዌሩ በኮሌጁ መምህራን እና በመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የተዘጋጀ ሲሆን አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማድረግ ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ ዳይሬክተሩ ከዚህ ቀደም ባለው ልምድ ሥርዓተ ትምህርት ክትትል የሚደረገው ኮርስ ከተጠናቀቀ በኋላ መሆኑን አስታውሰው ሶፍትዌሩ ኮርሱ እየተሰጠ ባለበት ጊዜ ለመከታተል እና መረጃን በወቅቱና በትክክል ለመያዝ የሚረዳ ሲሆን መረጃዎችን በየቀኑና በየሳምንቱ ሰብስቦ በመገምገም መምህራን በሠሩት ልክ ነጥብ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ የነጥብ አሰጣጡን በተመለከተ ከ80 በላይ አረንጓዴ፣ ከ50-79 ቢጫ እና ከ50 በታች ሲሆን ቀይ የሚያበራ መሆኑን ያብራሩት ዳይሬክተሩ ሶፍትዌሩን በመጠቀም ጥራቱን የጠበቀ መማር ማስተማር ማስፈን እና ዩኒቨርሲቲውን ተመራጭ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ትምህርት ጥራት አስተባባሪ ዶ/ር ሕይወት ጸጋዬ መምህራን ኮርሶችን በአግባቡ እየተገበሩ መሆኑን በመከታተል የትምህርት አሰጣጥ ጥራትን ለማስጠበቅ ሶፍትዌሩ ወሳኝ መሆኑን ተናግረው ለተግባራዊነቱ ሁሉም የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት