በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ የተሠራው የሕጻናት ማቆያ ማዕከል የምረቃና ሥራ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ኅዳር 20/2017 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዳምጠው ዳርዛ (ዶ/ር) የሰው ልጅ ዕድገትን የተሻለ እንዲሆን ማስቻል የትምህርት ተቋማት ዋነኛ ተግባር መሆኑን ገልጸው ከዚህ አንጻር አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከአፀደ ሕጻናት እስከ 3ኛ ዲግሪ ባሉ የትምህርት ደረጃዎች በርካታ ዜጎችን አሠልጥኖ ለሀገር እያበረከተ ይገኛል ብለዋል። በማዕከሉ በሚገቡ ሕጻናት ላይ ከአሁን ጀምሮ መስራት በሕጻናቱ የወደፊት ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ትልቅ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ያሉት ዶ/ር ዳምጠው እንደ ዩኒቨርሲቲያችን መሪ ቃል ሁሉ የወደፊት የሕጻናቱ ሕይወት ብሩህ እንዲሆን ማዕከሉ በትልቁ የሚረዳ እንደሆነ ጠቁመዋል። ከዚህ አንጻር  ማዕከሉ የሚጠበቅበትን አገልግሎት በጥራት አንዲሰጥ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበው ለማዕከሉ ተጠናቆ መመረቅ የበኩላቸውን ለተወጡ በዩኒቨርሲቲው ለሚገኙ የሥራ ከፍሎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የአስተዳደርና ልማት ም/ሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን ማዕከሉ በተለይ ለእናቶች ትልቅ እረፍትና እፎይታ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረው ማዕከሉ ከዚህ በተሻለ ምቹና ማራኪ እንዲሆን የማድረግና በቀሪ ግብአት የማሟላት ሥራ በቶሎ ይሠራል ብለዋል። የሕጻናት ማቆያ ማዕከላት በሁሉም ካምፓሶች ሊኖሩን ይገባል ያሉት ም/ፕሬዝደንቷ ማዕከላቱ በሌለባቸው ካምፓሶች ተጨማሪ ማዕከላትን ለማቋቋም እንደሚሠራም አውስተዋል። 

የዩኒቨርሲቲው ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ በበኩላቸው በአብዛኛው ሴት መምህራን፣ ተመራማሪዎችና ሠራተኞች ካለባቸው ሕጻናትን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት ሙሉ ትኩረታቸውንና አቅማቸውን በተሰማሩበትና በተመደቡበት የሥራ መስክ ላይ ለማድረግ ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ ለሴቶች ስኬታማነት፣ ለሕጻናት ደኅንነትና ጤንነት እንዲሁም ለተቋማችን ውጤታማነት የማዕኩሉ ሥራ መጀመር ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የመሰል ማዕከላት በግቢ ውስጥ መኖር እናቶች ልጆቻቸውን በቅርበት እየተከታተሉ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲሠሩና ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዝ መሆኑንም ሥራ አስፈጻሚዋ አክለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የማዕከሉ መኖር ሕጻናት ተገቢውን እንክብካቤ በእናቶቻቸው የቅርብ ክትትል ውስጥ ሆነው እንዲያገኙ በማድረግ በሕጻናት ጤንነት፣ ዕድገትና ደህንነት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታልም ብለዋል፡

የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች ለማዕከሉ መጠናቀቅና ለሥራ ዝግጁ መሆን ድርሻቸውን ለተወጡ የሥራ ክፍሎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ከልጆች ደኅንነት፣ በማዕከሉ አንዲሠሩ የተመደቡ ባለሙያዎችና ሞግዚቶች ኃላፊነት፣ እንዲሁም የመሰል ማዕከላት በሌሎች ካምፓሶች መስፋፋት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ በአስተያየታቸው ገልጸዋል፡፡ 

በማዕከሉ አንዲሠሩ የተመደቡ ባለሙያዎችና ሞግዚቶች በአምዩ አይ ዩ ሲ ፕሮጀክት አማካይነት ሥልጠና የወሰዱ መውሰዳቸው እና ማዕከሉ ዕድሜያቸው ከ4 ወር እስከ 3 ዓመት ያሉ 45 ሕጻናትን ተቀብሎ የማስተናገድ አቅም ያለው መሆኑ በመርሃ ግብሩ ላይ ተጠቁሟል፡፡


አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት