የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል ከደረጃ ዶት ኮምና ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተበባበር ‹‹Dereja. Com Campaign 2024/25›› በሚል ርእስ ደረጃ ዶት ኮም በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ዙሪያ ለ2017 ተመራቂ ተማሪዎች ከጥቅምት 7-9/2017 ዓ.ም ገለጻ አድርጓል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጂ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ ደረጃ ዶት ኮም በቀጣሪ ድርጅትና በሥራ ፈላጊ ወጣቶች መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ የሥራ ዕድል እንዲያገኙና ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ እየሠራ ያለ ትልቅ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ያለንበት ጊዜ ውድድር የሞላበትና ዲጂታል ዓለም ነው ያሉት ዲኑ በትምህርት የተሻለ ውጤት ይዞ መመረቅ የውድድሩ አንዱ መስፈርት ቢሆንም ውጤታማ ለመሆን ሥልጠናውን በአግባቡ በመውሰድ ራሳቸውን ለሥራ ብቁ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል አስተባባሪ መ/ርት ስለእናት ድሪባ በበኩላቸው ደረጃ ዶት ኮም ከዚህ ቀደም ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች በተጨማሪ አምስት ፓኬጆችን እያስተዋወቀ እንደሚገኝ ገልጸው ተማሪዎች ከ‹‹Dereja Academy Accelerator Program (DAAP)›› እና ‹‹Employability Skills›› በተጨማሪ የፈለጉትን ፓኬጅ መርጠው ሥልጠናውን መውሰድ እንደሚችሉ ለማሳወቅ የሚደረግ ገለጻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው ተማሪዎች ተመርቀው ከወጡ በኋላ ሥራ በማፈላለግ የሚያጠፉትን ጊዜ በመቆጠብ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑና የሥራ ዕድል እንዲያገኙ የሚረዳ ስለሆነ ተማሪዎች ያላቸውን ጊዜ በአግባቡ በመጠቀም ሥልጠናውን እንዲወስዱ አስተባባሪዋ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በደረጃ ዶት ኮም የቁጥጥርና ምዘና ማኔጀር /Monitoring and Evaluation Manager/ መ/ርት የጣናወርቅ በቀለ በደረጃ ዶት ኮም ከዚህ ቀደም ከሚሰጡ አገልግሎቶች በተጨማሪ ‹‹Career Campus››፣ ‹‹Internship››፣ ‹‹Technical skill››፣ ‹‹Digital Skills Training Dereja.com(digital Portal)፣ ‹‹Career Orientation and Job Readiness›› እና ‹‹Job Fair and Career Expos›› የሚሉ ተጨማሪ ፓኬጆች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ምሩቅ ወጣት ኤደን ተስፋዬ ተሞክሮዋን ለተማሪዎች ያቀረበች ሲሆን አሁን ላይ በትምህርት ዓለም በተገኘ ዕውቀት ብቻ ሥራ ማግኘት ከባድ መሆኑን ተናግራለች፡፡ ከዚህ ቀደም ደረጃ ዶት ኮም ባወጣው ማስታወቂያ ሥልጠና በመውሰድ ሰዋዊና ሙያዊ ክሂሎቶችን ማዳበር በመቻሏ በተወዳደረችበት ዘርፍ ሥራ መያዟን ተናግራለች፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት